ኢትዮጵያ በስንዴ ልማት ያስመዘገበችው ስኬት ለአፍሪካውያን በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በስንዴ ልማት ያስመዘገበችው ስኬት ለአፍሪካውያን በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው
አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 6/2018(ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በስንዴ ልማት ያስመዘገበችው ስኬት ለአፍሪካዊያን በምሳሌነት የሚጠቀስ መሆኑን የአፍሪካ አረንጓዴ አብዮት ጥምረት ቦርድ ሊቀ መንበር ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ።
የአፍሪካ አረንጓዴ አብዮት ጥምረት የተመሰረተበትን 20ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የከፍተኛ ባለሙያዎችና የሥራ ኃላፊዎች ውይይት እየተካሄደ ነው።
የአፍሪካ አረንጓዴ አብዮት ጥምረት (አግራ) የአነስተኛ አርሶ አደሮችን በግብዓትና በቴክኖሎጂ በመደገፍ የግብርና እድገትን ለማሳለጥ እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጣር በ2006 የተመሰረተ አፍሪካ መር ተቋም ነው።
ተቋሙ የተሻሻለ የዘር ብዜትን፣ የአፈር ጤናማነትን በማስጠበቅና ለግብርና ምርቶችን የገበያ ዕድል በማመቻቸት ዘርፉን በማዘመን የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ግብ ይዟል።
የኢትዮጵያ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትርና የአፍሪካ አረንጓዴ አብዮት ጥምረት ቦርድ ሊቀ መንበር ኃይለማርያም ደሳለኝ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት፤ ግብርና ለአፍሪካ የምግብ ዋስትና እና የኢኮኖሚ ዕድገት ለማረጋገጥ የጀርባ አጥንት ነው።
አግራ ከ20 ዓመት በፊት ሲቋቋም ለአፍሪካ የስርዓተ ምግብ ዕጣ ፋንታ ወሳኝ የሆነውን ግብርና በማዘመን የዜጎችን ምርታማነት ለማሳደግ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።
ግብርና ለአፍሪካ ብልፅግና መሰረት መሆኑን ገልጸው፤ ለስኬታማነቱ የተቋማት ትብብርና ግልፅ የፖሊሲ አተገባበር ያስፈልጋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የግብርና ኤክስቴንሽን ስርዓት በማጠናከርና ቁርጠኛ አመራር በመስጠት ምርትና ምርታማነትን በማሻሻል የወጭ ንግዷን ማሳደግ መቻሏን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ምርትና ምርታማነት እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ በስንዴ ልማት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች በምሳሌነት የሚጠቀስ ስኬት አስመዝግባለች ብለዋል።
ኢትዮጵያ በሰብል ልማት ብቻ ሳይሆን በእንስሳት ሀብት እና ሌሎች የግብርና ዘርፎች የአርሶ አደሮችን ተሳትፎ በማሳደግ በአህጉሪቷ ተጠቃሽ ለውጥ ማምጣቷን ገልጸዋል።
በአፍሪካ የግብርና ሽግግር በመፍጠር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና ዘላቂ እድገትን ለማስፈን ለችግሮች መፍትሔ ማፈላለግ እንደሚገባም ተናግረዋል።
በአፍሪካ የምግብ ስርዓትን ብሔራዊ አጀንዳ ማድረግ ይገባል ያሉት የቦርዱ ሊቀ መንበር፤ አግራ የአፍሪካ ግብርና ሽግግር አቀጣጣይ ሆኖ እያገለገለ ነው ብለዋል።
አርሶ አደሩ ዘላቂ የአሰራር ስርዓት እንደሚፈልግ ገልጸው፤ ለሥርዓቱ ቀጣይነት ያለው የተቋማት ትብብር እንደሚያስፈልግ በአጽንኦት ገልጸዋል።
በአፍሪካ ህብረት የገጠር ልማት ክፍል እና የግብርናና ምግብ ዋስትና ዘርፍ ኃላፊ ጃኔት ኢደሜ (ዶ/ር)፤ ህብረቱ የምግብ ስርዓትን አሕጉራዊ አጀንዳ አድርጎ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በአፍሪካ የግብርና ሽግግር ለመፍጠርና የማህበራዊ ዋስትናን ለማረጋገጥ በትብብር መስራት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
የግብርና ሽግግር የኢኮኖሚ ዕድል ብቻ አይደለም ያሉት ኃላፊዋ፤ የደህንነትና ሉዓላዊነት ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህ ደግሞ አካታች፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር፣ ጠንካራ ተቋማት መገንባትና የፖሊሲ ማዕቀፍ ማውጣት እንደሚገባ አመልክተዋል።
የአፍሪካን ትርክት በፈጠራና በጥምረት መገንባት እንደሚገባ ገልጸው፤ ታሪክ ያለፈ ብቻ ሳይሆን ነገን መገንባት ጭምር መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይ 20 ዓመታት አርሶ አደሮችን በማጠናከር ግብርናን ለአፍሪካ ዘላቂ ዕድገትና ልማት መጠቀም እንደሚገባ አብራርተዋል።