ቀጥታ፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር ለግብርና ምርትና ምርታማነት ገንቢ ሚና እየተወጣ ነው

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 6/2018(ኢዜአ)፡-የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የምግብ ስርዓትን በማሻሻል፤ ገበያን በማሳደግና ሥነ ምህዳርን በመመለስ ለግብርና ምርትና ምርታማነት ገንቢ ሚና እየተወጣ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር ኢያሱ ኤልያስ ገለጹ።

የአፍሪካ አረንጓዴ አብዮት ጥምረት /አግራ/ የተመሰረተበትን 20ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የከፍተኛ ባለሙያዎችና የሥራ ሀላፊዎች ውይይት ተካሄዷል።


 

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር ኢያሱ ኤልያስ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ በአፍሪካ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ዘላቂ ዕድገት ለማስመዝገብ የግብርና ሽግግር ወሳኝ ነው።

የግብርና ሽግግርን ለማረጋገጥ ደግሞ ለአርሶ አደሩ ዘላቂ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን መፍጠር ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የግብርና ሜካናይዜሽንን በማሳደግ፣ ጠንካራ የፖሊሲ ርምጃ በመከተልና ቁርጠኛ አመራር ውሳኔ በመስጠት በግብርናው ዘርፍ እመርታዊ ለውጥ ማስመዝገቧን ገልጸዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀዳሚ የስንዴ አምራችና ከፍተኛ የቡና ምርት ላኪ መሆን መቻሏን ገልጸው፤ የመስኖ ልማትና የኤክስቴንሽን ስራዎች ውጤት አበርክቶ የላቀ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ግብርና የአግሮ ፎረስትሪ ስትራቴጂ እና ሌሎች ኢንሼቲቮችን በመጀመር የምርት ስርዓቱ እንዲቀየር፣ የትራክተርና ኮምባይነር ግብዓት በዕጅጉ እንዲሻሻል መደረጉን ገልጸዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አካባቢን በመጠበቅ፣ ገበያን በማሳደግና የምግብ ስርዓትን በማሻሻል ለግብርና ምርትና ምርታማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገርና በቴክኖሎጂ የታጠቀ የግብርና ሥርዓት እየተገበረች መሆኑንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ ሽግግር በመፍጠር የገጠር ሽግግር፣ ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገትና የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ግብ ይዛ እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል።

አግራ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም በሚያስችሉ ስራዎች ላይ በማማከር፣ በመስኖ ልማትና የተሻሻለ ግብርና ላይ በማተኮር ለአነስተኛ አርሶ አደሮች ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የአፍሪካ አረንጓዴ አብዮት ጥምረት /አግራ/ ፕሬዝዳንት አሊዝ ሩዌዛ በበኩላቸው፤ በአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጫና እና የዜጎች የምግብ ፍላጎት መጨመር ትርጉም ያለው የኢኮኖሚ እድል መፍጠርን ይጠይቃል ብለዋል፡፡


 

በተለይም የወጣቶችን ተጠቃሚነት ማሳደግ ፈጣን ምላሽ የሚያስፈልገው መሆኑን ጠቅሰው፤ በትብብርና በትኩረት መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በጠንካራ አመራርና ውሳኔ ሰጭነት በግብርናው ዘርፍ ስኬት አስመዝግባለች ያሉት ፕሬዝዳንቷ፤ በምርምር፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ የተደገፉ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል፡፡

የአፍሪካ አረንጓዴ አብዮት ጥምረት /አግራ/ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ይሄነው ዘውዴ (ዶ/ር)፤ ባለፉት 20 ዓመታት ከኢትዮጵያ ጋር በጠንካራ ትብብር መስራታቸውን ገልጸዋል።


 

አግራ ጥምረት በመሆኑ በትብብር ያምናል ያሉት ዳይሬክተሩ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ባለሙያዎችን በማሰማራት ሲሰራ መቆየቱንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም