የሴቶችን የንግድ ዘርፍ ተሳትፎ በማሳደግ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሴቶችን የንግድ ዘርፍ ተሳትፎ በማሳደግ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 6/2018 (ኢዜአ)፡-ሴቶች በንግድ ዘርፍ ያላቸውን ተሳትፎ በማሳደግ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት በተጠናከረ መንገድ እየተከናወኑ መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
በሥርዓተ ጾታ እኩልነትና የሴቶች ተጠቃሚነት ላይ ትኩረቱን ያደረገው 15ኛው የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ሀገራት የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) ሴክሬታሪያት የቴክኒካል ኮሚቴ አህጉራዊ ስብሰባ መካሄድ ጀምሯል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሂክማ ኸይረዲን በዚህ ወቅት፤ኢትዮጵያ የገጠርና የከተማ ሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ልዩ ልዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ ትገኛለች ብለዋል።
የሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ስትራቴጂ ተቀርፆ ወደ ተግባር መገባቱን አውስተው፤በዚህም በግብርና፣በኢንዱስትሪ፣በስራ እድል ፈጠራና በሌሎች ዘርፎች ላይ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል።
የአፍሪካውያን ሴቶችን በንግድ ስርዓቱ ላይ ተሳታፊና እኩል ተጠቃሚ ለማድረግ በትብብር መስራት እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
ሴቶች በንግድ ላይ ለመሳተፍ ማነቆ የሆኑባቸውን ተግዳሮት በመፍታት ውጤታማ እንዲሆኑ ለማስቻል የኮሜሳ አባል ሀገራት ተቀራርበን መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
የዛሬው ምክክርም ይህን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ነው የተናገሩት።
ውይይቱ አፍሪካውያን ሴቶች በንግድ ስርዓቱ ላይ ያላቸውን ተጠቃሚነት ማሳደግ የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ በማዘጋጀት ወደ ተግባር መቀየር የሚቻልበትን እድል የሚፈጥር መሆኑን አንስተዋል።
የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ሀገራት የጋራ ገበያ(ኮሜሳ) ረዳት ፀሀፊ አምባሳደር ማህመድ ካዳ በበኩላቸው፤ኢትዮጵያ የሥርዓተ ፆታ እኩልነትንና የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማስፈን ለምታሳየው የአመራር ቁርጠኝነት አመሰግነዋል።
እንደ አህጉር የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚሰሩ ስራዎች አበረታች ቢሆንም ቀሪ ስራዎች መኖራቸውን አንስተዋል።
በተለይም በአፍሪካ ሴቶች የፋይናንስ፣የዲጂታል ክህሎት፣ የገበያ፣ የውሳኔ ሰጪነት ያላቸውን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አንፃር ክፍተቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
15ኛው የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ሀገራት የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) ሴክሪቴሪያት ቴክኒካል ኮሚቴ አህጉራዊ ስብሰባ እነዚህን ክፍተቶች ለመሙላት ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል፡፡