በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምጽ መስጠት የሚያስችለንን የምርጫ ካርድ ውስደናል-የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምጽ መስጠት የሚያስችለንን የምርጫ ካርድ ውስደናል-የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪዎች
ወላይታ ሶዶ፤ ሚያዝያ 6 /2018(ኢዜአ)፡- በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምጽ መስጠት የሚያስችላቸውን የምርጫ ካርድ መውሰዳቸውን የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመጪው ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ለሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ እስከ ሚያዝያ 14 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ማራዘሙ ይታወሳል።
ቦርዱ የምርጫ ሂደቱ አሳታፊና አካታች እንዲሆን ባሳወቀው ተጨማሪ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት የመራጮች ምዝገባ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ቀጥሏል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪዎች የምዝገባው ጊዜ መራዘሙ፣ በተለያዩ ምክንያቶች ካርድ መውሰድ ላልቻሉ ዜጎች መልካም አጋጣሚ መፍጠሩን ተናግረዋል።
ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ምልኪያስ ወልዴ "በምርጫው ድምፄን ለመስጠት ተመዝግቤ ካርድ ወስጃለሁ'' ይላሉ።
''የእኔ ድምፅ በተሻለ መልኩ ሀገርን የሚመራ ፓርቲ ወደ ሥልጣን እንዲመጣ ጉልህ ድርሻ እንዳለው ስለማምን ዴሞክራሲያዊ መብቴን ለመጠቀም ተዘጋጅቻለሁ" ብለዋል።
ሌላዋ ወይዘሮ ተስፋነሽ ግርማ፣ ምርጫ የዜግነት ግዴታን ለመወጣትና ዴሞክራሲያዊ መብትን ለመጠቀም ሁነኛ መሣሪያ በመሆኑ፣ ካርድ ያልወሰዱ ዜጎች ጊዜው ሳይጠናቀቅ ካርድ ወስደው መዘጋጀት አለባቸው ብለዋል።
አቶ መልካሙ ለማ በጊዜ ሰሌዳው መሠረት ካርድ ወስደው መዘጋጀታቸውን ተናግረው፣ የሀገሪቱን ልማት የሚያፈጥን የፖለቲካ ፓርቲ በመምረጥ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ለመጠቀም መዘጋጀታቸውን አስረድተዋል።
ነዋሪዎቹ፣ ምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና አካታች ሆኖ እንዲጠናቀቅ የድርሻቸውን ለመወጣትና ለሚፈልጉት የፖለቲካ ፓርቲ ድምፅ ለመስጠት የምርጫ ካርዳቸውን በአግባቡ ይዘው የምርጫውን ቀን እየተጠባበቁ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።