በኦሮሚያ ክልል በመስኖ ልማት የአርሶ አደሩን የስራ ባህል መለወጥ ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል በመስኖ ልማት የአርሶ አደሩን የስራ ባህል መለወጥ ተችሏል
አዲስ አበባ ሚያዝያ 6/2018(ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል ለመስኖ ልማት በተሰጠው ትኩረት በአርሶ አደሩ ዘንድ 'ክረምት አርሶ በጋ ማረፍ' የሚለውን አመለካከት መለወጥ መቻሉን የክልሉ የመስኖ እና አርብቶ አደር ልማት ቢሮ ገለጸ።
የቢሮው ኃላፊ ኢንጂነር ግርማ ረጋሳ፤ የክልሉ መንግሥት ባለፉት የለውጥ ዓመታት ግብርናን ለማዘመን የሚያስችሉ ውጤታማ ተግባራትን አከናውኗል ብለዋል።
ከእነዚህ ሥራዎች መካከል ቀደም ሲል እምብዛም ትኩረት ያልተሰጠውን የመስኖ ልማት ሥራ በመሠረታዊነት መለወጥ ያስቻሉ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በተለይም በክልሉ ቆላማ አካባቢዎች በተከናወኑ የመስኖ ልማት ሥራዎች የአርብቶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ጭምር እያገዘ መሆኑን ተናግረዋል።
የክልሉ መንግሥት የመስኖ ልማትን ለማስፋፋት ዘመናዊ የመስኖ አጠቃቀምን ማዳበርና አነስተኛ እና መለስተኛ የመስኖ ግድቦች ግንባታን ማከናወን መቻሉንም ጠቁመዋል።
ይህ ብቻ ሳይሆን የክልሉ መንግስት 3 ቢሊዮን ብር በጀት በመመደብ የውኃ መሳቢያ ሞተሮችን ጨምሮ ለመስኖ ልማት የሚያግዙ ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ እና አርብቶ አደሩ እንዲቀርቡ መደረጉን አስረድተዋል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት ብቻ ከ200 በላይ የመስኖ መሠረተ ልማቶች መገንባታቸውን ጠቅሰው፤ "ፊነ" በተሰኘ በክልሉ ቆላማ አካባቢ ልማት ላይ በሚሠራ ፕሮጀክት አማካኝነትም የተሻለ ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል።
በ"ፊነ" ፕሮጀክት አማካኝነት በክልሉ ቆላማ እና አርብቶ አደር አካባቢዎች የተገነቡ የውሃ ጉድጓዶችና አነስተኛ እና መለስተኛ የመስኖ ግድቦች ትልቅ ተስፋ የሰጡ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
ለአብነትም በቦረና አካባቢ የተገነቡ አነስተኛ እና መለስተኛ የመስኖ ግድቦች አርብቶ አደሩ ማኅበረሰብ ድርቅን መቋቋም እንዲችል እያገዙት ሲሆን፤ ለእንስሳት መጠጥ እና ለመኖ ልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ ብለዋል።
በአጠቃላይ በክልሉ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ ሥራዎች 70 ሺህ ሄክታር የነበረው የመስኖ ልማት ሽፋን በዚህ ወቅት ከ3 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መድረሱን ገልጸዋል።
ከሁሉም በላይ የክልሉ መንግሥት ለመስኖ ልማት በሰጠው ልዩ ትኩረት በአርሶ አደሩ ዘንድ የነበረውን "ክረምት አርሶ በጋ የሚያርፍበትን" አሮጌ አመለካከት መለወጥ ተችሏል ብለዋል።
በዚህም የክልሉ አርሶ እና አርብቶ አደር ዓመቱን ሙሉ የግብርና ሥራ እያከናወነ የምግብ ዋስትናውን ማረጋገጥ እንዲችል የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ጠቁመዋል።