ቀጥታ፡

ለዘላቂ ሰላም፣ ልማትና ለዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ የተሻለ ይሰራል ያልነውን ፓርቲ ለመምረጥ ካርድ ወስደናል

ገንዳውኃ፣ ሚያዝያ 6/2018 (ኢዜአ)፡- ለዘላቂ ሰላም፣ ልማትና ለዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ የተሻለ ይሰራል ያሉትን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ የሚያስችላቸውን ካርድ መውሰዳቸውን በምዕራብ ጎንደር ዞን የኮኪትና ገንዳ ውሀ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ ።

ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን በመገንባት የህዝብን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ  ወሳኝ ሚና እንዳለው ይታወቃል።

ለዚህም ህዝቡ በሂደቱ በንቃት በመሳተፍ መብትና ግዴታውን  ሊወጣ እንደሚገባ ይታመናል ።

የኢትዮጵያ ዜና  አገልግሎትም በዚሁ ጉዳይ ላይ በምዕራብ ጎንደር ዞን የኮኪትና ገንዳ ውሀ ከተማ ነዋሪዎችን ያነጋገረ ሲሆን ነዋሪዎቹም ለዘላቂ ሰላም፣  ልማትና ዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ የተሻለ ይሰራል ያሉትን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ ካርድ መውስዳቸውን ተናግረዋል ።

በዞኑ መተማ ወረዳ  የኮኪት ከተማ  ነዋሪ አቶ ሲሳይ ደሴ  በምርጫው በንቃት  በመሳተፍ ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ የበኩላቸውን ለመወጣት የምርጫ ካርድ መውሰዳቸውን ገልጸዋል። 

የሀገር  ልማትና ሰላም  ለማስቀጠል  በምርጫው በንቃት መሳተፍና  የድምፅ መስጫ ካርድን መያዝ ወሳኝ መሆኑን ገልፀው በተለያዩ አማራጮች የሚተላለፈውን  የምርጫ ቅስቀሳ እየተከታተሉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ሌላው በኮኪት ምርጫ ጣቢያ የመራጭነት ካርድ የወሰዱት አቶ ምስጋናው አለኸኝ በበኩላቸው፤ የአካባቢውን ሀብትና ፀጋ ተጠቅሞ የህዝቡን ተጠቃሚነት ሊያረጋግጥ የሚችል ፓርቲን ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል። 

እንዲሁም የአካባቢውን የሰላም ሁኔታ በዘላቂነት የሚያሻሽል የህዝቡን መሰረታዊ ጥያቄዎች መመለስ የሚችል ፓርቲን እንደሚመርጡ አረጋግጠዋል። 

በቅድመ ምርጫ ያለው ሰላማዊ ሂደት በምርጫ እለትና ከምርጫ በኋላ አስተማማኝ ሆኖ እንዲዘልቅ የድርሻቸውን እንደሚወጡም አመላክተዋል።

ምርጫው ሰላማዊና ፍትሀዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የህዝቡ ድርሻ  ከፍተኛ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ የበኩላቸውን እየተወጡ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ  ​በዞኑ  የገንዳውሃ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ሞሚና ዑመር ናቸው። 

ሰላምን  ለማስፈንና የህዝብን  የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን የሚፈታ የፖለቲካ ፓርቲን ለመምረጥ ቀድመው ካርድ መያዛቸውን ተናግረዋል። 

"ምርጫ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት መፍትሄ መሆኑን አምነን ካርዳችንን በእጃችን ይዘናል" ያሉት ደግሞ ሌላው የገንዳ ውሀ ከተማ ነዋሪ አቶ ገብሬ አዱኛ ናቸው። 

በምርጫው የሚኖራቸው ተሳትፎ ለዴሞክራሲ ግንባታ ወሳኝ መሆኑን በመገንዘብ በምርጫው እለት ይመራኛል ለሚሉት የፖለቲካ ፓርቲ ድምጻቸውን በመስጠት ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ  አመላክተዋል። 

​በምዕራብ ጎንደር ዞን የምርጫ ጣቢያ አስተባባሪዎች በበኩላቸው፣ የካርድ መስጠት ሂደቱ በሰላማዊ መንገድ እየተከናወነ መሆኑንና ህብረተሰቡም በንቃት እየተሳተፈ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። 

ጠቅላላ ምርጫው ኢትዮጵያ የጀመረችውን  የዴሞክራሲ ጉዞ ለማጠናከርና የተረጋጋ የፖለቲካ ስርዓት ለመፍጠር ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ይጠበቃል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም