በዞኑ በበልግ ወቅቱ ከ92 ሺህ 400 ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ዘር ተሸፍኗል - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ በበልግ ወቅቱ ከ92 ሺህ 400 ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ዘር ተሸፍኗል
ደሴ፤ ሚያዚያ 6/2018 (ኢዜአ)፡- በደቡብ ወሎ ዞን እየጣለ ያለውን የበልግ ወቅት ዝናብ በመጠቀም ከ92 ሺህ 400 ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ዘር መሸፈኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡
በመምሪያው የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ ይመር ሰይድ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዞኑ የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ ነው።
በዚህም በበልግ ወቅቱ ከ104 ሺህ 600 ሄክታር በላይ መሬት በማልማት ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
እስካሁን በተደረገ ጥረት ከ92 ሺህ 400 ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ዘር መሸፈኑን ጠቁመው ከተዘራው ውስጥ ስንዴ፣ ገብስ፣ ጤፍ፣ ቦለቄ፣ ማሾ፣አተር፣ ምስርና ሌሎች ሰብሎች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።
እቅዱን ለማሳካትም እስከ ሚያዚያ 15 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ፈጥነው የሚደርሱ ሰብሎች ላይ በማተኮር የዘር ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉን አስገንዝበዋል።
በቀጣይም አርሶ አደሩ የሰብሉን ሁኔታ በመከታተል የአረምና የተባይ ቁጥጥር ስራ እንዲያከናውን የባለሙያ ድጋፍ እንደሚደረግ አመላክተዋል።
የበልግ ልማቱን ምርታማነት ለማሳደግም ለአርሶ አደሩ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ቀድሞ መቅረቡን ተናግረዋል።
በዞኑ ተሁለደሬ ወረዳ የቀበሌ 01 ነዋሪ አርሶ አደር አህመድ መሀመድ በበኩላቸው፣ የዘንድሮው የበልግ ዝናብ ለሰብል ልማት ምቹ በመሆኑ አንድ ሄክታር ተኩል ማሳቸውን በስንዴና በጤፍ ማልማታቸውን ጠቁመዋል።
ለስራው ስኬትም የግብርና ግብዓት በወቅቱ ማግኘታቸውን ጠቁመው ሰብሉን በተገቢው በመንከባከብ ጥሩ ምርት እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።
እየጣለ ያለውን የበልግ ዝናብ በመጠቀም አንድ ሄክታር ማሳቸውን በስንዴና ገብስ ዘር መሸፈናቸውን የተናገሩት ደግሞ በኩታበር ወረዳ የቀበሌ 03 ነዋሪ አርሶ አደር ይመር ሰይድ ናቸው።
የሰብሉ ቡቃያ ያማረ በመሆኑ ከአረምና ከተባይ የመጠበቅ ስራ እያከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል።