ቀጥታ፡

የበጋ ስንዴ ልማት አርሶ አደሩ ከራሱ ፍጆታ አልፎ ለገበያ የሚሆን ምርት ለማቅረብ አስችሏል

ጎንደር ፤ሚያዚያ 6/2018 (ኢዜአ)፡-በማእከላዊ ጎንደር ዞን የተካሔደው የበጋ ስንዴ ልማት ስራ አርሶ አደሩ ከራሱ ፍጆታ አልፎ  ለገበያ የሚሆን ምርት ለማቅረብ ማስቻሉን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡

በዞኑ ዘንድሮው በተካሄደው የበጋ ወቅት የመስኖ ስንዴ ልማት ስራ ከአንድ ሚሊዮን ኩንታል በላይ የስንዴ ምርት ለገበያ ማቅረብ መቻሉም ተገልጿል፡፡

በመምሪያው የመስኖ ልማት ቡድን መሪ አቶ ሀውልቱ ታደሰ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ኢንሼቲቭ አርሶ አደሩ ዓመቱን ሙሉ የሚያመርትበትን አዲስ የስራ ባህል ፈጥሯል። 

በዞኑ ከአራት ዓመት በፊት በበጋ መስኖ ስንዴ የሚለማው መሬት ከአራት ሺህ ሄክታር የማይበልጥ፤የሚገኘው ምርት ደግሞ  ከ112 ሺህ ኩንታል የዘለለ እንዳልነበረ አስታውሰዋል።  

በዘንድሮ የበጋ ወቅት ደግሞ ከ29 ሺ ሄክታር በላይ መሬት በማልማት ዓመታዊ ምርቱን ከአንድ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ለማድረስ  መቻሉን ገልጸዋል።

የበጋ ስንዴ ልማት ስራ አርሶ አደሩ ከራሱ ፍጆታ ባለፈ ለአግሮ ኢንዱሰትሪዎች ግብአትና ለገበያ የሚሆን ምርት በማምረት ተጠቃሚነቱን ለማሳደግ ማስቻሉን ነው የገለጹት፡፡

በዚሁ ወቅት አርሶ አደሩ ምርታማነትን እንዲያሳድግም አዳዲስና ዘመናዊ የግብርና አሰራሮችንና ቴክኖሎጂዎችን በስፋት ተግባራዊ እንዲያደርግም የባለሙያዎች እገዛ ከፍተኛ አስተዋጽአ ማበርከቱን ነው የተናገሩት።

የኩታ ገጠም እርሻ፤ የአፈር ማዳበሪያና ምርጥ ተሞክሮችን በመጠቀም በዘላቂነት ምርታማነትን ለማሳደግ እንዲቻል  በትኩረት መሰራቱን አስረድተዋል።  

በዞኑ የወገራ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር መላኩ ቸርነት ፤ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ስራ ለራስ ፍጆታ ብቻ የነበረውን አመራረት በመቀየር ለገበያ የሚተርፍ ምርት ማግኝት  እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።

በዘንድሮ በጋም በአንድ ሄክታር መሬት ካለሙት የስንዴ ሰብል 36 ኩንታል ስንዴ በማምረት ለገበያ አቅርበው ተጠቃሚ መሆናቸውን ነው የሚገልጹት፡፡

በምእራብ ደንቢያ ወረዳ የዋዋ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር የሻምበል መንግስቱ በበኩላቸው፤ በዘንድሮው በጋ በግማሽ ሄክታር መሬት  ላይ በመስኖ ካለሙት የሰንዴ ሰብል 18 ኩንታል ምርት አግኝተዋል።

ያገኙት ምርትም ከራሳቸው አልፎ ለገበያ ለማቅረብ መቻላቸውን ነው ያስታወቁት።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም