ቀጥታ፡

በሐረሪ ክልል በሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር አበረታች ውጤት ተመዝግቧል

ሐረር ፤ ሚያዝያ 06/2018 (ኢዜአ) ፦ በሐረሪ ክልል እየተከናወነ ባለው የሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር አበረታች ውጤት መመዝገቡን የክልሉ ግብርና ልማት ቢሮ አስታወቀ።

በቢሮው የእንሰሳት ሃብት ልማት ዳይሬክተር ናኦል አብዱማሊክ ለኢዜአ እንደገለጹት ባለፉት ዓመታት በሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር በተከናወኑ ተግባራት በእንስሳት ሀብት ልማትና ምርታማነት ላይ አበረታች ውጤት ተመዝግቧል።


 

በዚህም የወተት ምርትን በማሳደግ፣ የእንቁላልና የማር ምርት አቅርቦትን በማሻሻል ረገድ ተጨባጭ ውጤት መታየቱን ጠቁመዋል።

የክልሉ መንግስት ከፍተኛ በጀት በመመደብ የሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብርን ማበረታታቱን አንስተው፤ በበጀት ዓመቱ ባለፉት 9 ወራትም 12 ሼዶችን በከተማና በገጠር በመገንባት ወደ ስራ መግባታቸውን ገልጸዋል።

እንዲሁም የእንስሳት መኖ አቅርቦትን የማጎልበት ተግባራት መከናወኑንም አብራርተዋል።

በዶሮ እርባታም በበጀት ዓመቱ 12ሺህ የዶሮ ጫጩቶችን ለህብረተሰቡ የማሰራጨት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው፤ በዚህም የህብረተሰቡ ፍላጎት እያደገ በመምጣቱ በራቱ ተነሳሽነት ግዢ እየፈጸመ መሆኑን አስረድተዋል።

ምርቱም በከተማው የቅዳሜና እሁድ ገበያ በተመጣጣኝ ዋጋ በስፋት እየቀረበ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

በክልሉ በሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር የተለያዩ ዘርፎች ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራቱ በዘርፉ የተሰማሩ አርሶ አደሮችና ሌሎች ግለሰቦች ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን ገልጸዋል።

በተለይም በዘርፉ ለወጣቶች የስራ እድል ከመፈጠሩ ባለፈ ገበያን በማረጋጋት ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም