ከተረጅነት ወደ ምርታማነት ፍኖተ ካርታ ትግበራ ድህነትን በመግታት ረገድ ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ከተረጅነት ወደ ምርታማነት ፍኖተ ካርታ ትግበራ ድህነትን በመግታት ረገድ ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ ነው
አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 6/2018 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ የተረጅነት ታሪክን ወደ ምርታማነት የማሸጋገር ፍኖተ ካርታ ትግበራ ድህነትን በመግታት ረገድ ውጤት እያስገኘ መሆኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሰማ ጥሩነህ (ዶ/ር) ገለጹ።
በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና በግብርና ሚኒስቴር ትብብር "ከተረጅነት ወደ ምርታማነት" በሚል መሪ ሃሳብ በአዳማ ከተማ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሰማ ጥሩነህ (ዶ/ር)፥ "ከተረጅነት ወደ ምርታማነት ለተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነትና ክብር" በሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ የመነሻ ጽሁፍ አቅርበዋል።
በመነሻ ጽሁፋቸውም፥ ኢትዮጵያ በቀደምት ጀግኖች ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ የቆየች ሀገር ናት ብለዋል።
ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ የቆየች ሀገር ብትሆንም ተረጅነትና ልመናን ለማስቀረት የነበረው የታሪክ ስብራት የተሟላ ሉዓላዊነትን ማጎናጸፍ ሳይችል እንደቆየ አስረድተዋል።
በዚህም ከሀገራዊ ለውጡ ማግስት የኢትዮጵያን የተሟላ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ የተወሰዱ የፖሊሲ እርምጃዎች ዜጎችን ክብር እያጎናጸፉ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በአየር ንብረት ለውጥና ተያያዥ ጉዳዮች ኢትዮጵያ በድርቅና ርሃብ አደጋ ፈተናዎችን በመቀልበስ እመርታዊ የምርታማነት ሽግግር መደረጉን ተናግረዋል።
የተረጅነት አስተሳሰብን ማስቀረትም ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ሉዓላዊነትና ክብር የላቀ ትርጉም የሚሰጠው መሆኑን አንስተዋል።
የራስ የምርታማነት አቅም በመፍጠር ለአደጋ የማይበገር ማህበረሰብ መገንባት እየተቻለ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
ይህም የኢትዮጵያን የተሟላ የሉዓላዊነት ፈተናዎች በመቀልበስ የተፈጠረው የምርታማነት አቅም የሀገርን አይበገሬነት በተግባር ያስመሰከረ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያን የተረጅነት ታሪክ ወደ ምርታማነት ለማሸጋገርም መግባባት፣ ማጥራት፣ ማዘጋጀት፣ ማቀናጀትና ማሸጋገር ፍኖተ ካርታ ትግበራ ድህነትን በመግታት ረገድ ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የልማታዊ ሴፍቲኔት መርሃ ግብርም በርካታ ዜጎችን ከድህነት በማላቀቅ የትርፍ አምራችነት ሽግግርን እያፋጠነ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በቀጣይም የብልፅግና ፓርቲ አመራርና አባላት፣የመንግሥት የስራ ኃላፊዎችና ሙያተኞች፣ የልማት አጋሮች፣ መገናኛ ብዙኅንና ህዝቡ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተመዘገበውን ስኬት የማስቀጠልና የማፅናት ኃላፊነታቸውን ማስቀጠል እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።