በክልሉ ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ስነ-ምህዳርን መሰረት ያደረገ የችግኝ ዝግጅት እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ስነ-ምህዳርን መሰረት ያደረገ የችግኝ ዝግጅት እየተከናወነ ነው
ባህርዳር፤ ሚያዚያ 6/2018 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል በመጪው ክረምት ለሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውና የአካባቢ ስነ-ምህዳርን መሰረት ያደረጉ ችግኞች እየተዘጋጁ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ እስመለዓለም ምህረት ለኢዜአ እንደገለፁት፤በመጭው የክረምት ወቅት የሚተከሉ አንድ ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ችግኞችን ለማዘጋጀት ታቅዶ እየተሰራ ነው።
እስካሁን በተደረገው ጥረትም ከአንድ ቢሊዮን በላይ ችግኞችን ማፍላት የተቻለ ሲሆን ቀሪውን ባጭር ጊዜ በማዘጋጀት ለተከላ ዝግጁ እንደሚደረግም ተናግረዋል።
ዝግጁ በመደረግ ላይ ያሉት ዋንዛ፣ ዝግባ፣ ኮሶ፣ ወይራ፣ ባህር ዛፍ ፣ የአበሻና የፈረንጅ ፅድ፣ አካሺያ ዲከረንስና ሌሎች ሀገር በቀልና የውጭ ዝርያ ያላቸው ችግኞች ናቸው ብለዋል።
ሊዚሁ የችግኝ ተከላ መርሃግብርም ከ200 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የመለየት ስራ መሰራቱንም አስገንዝበዋል።
በክልሉ ባለፈው የክረምት ወቅት ከተተከለው ከአንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን በላይ ችግኝ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው መጽደቁን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።