ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል ለዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር በርካታ ጥቅም ያላቸው ችግኞች እየተዘጋጁ ነው

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 6/2018 (ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል ለዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር ከ1 ሚሊዮን ሔክታር በሚልቅ አዲስ መሬት ላይ የሚተከሉ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች እየተዘጋጁ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በቢሮው የልማትና ደን እንክብካቤ ዳይሬክተርና የዘርፉ ተወካይ ከተማ አብዲሳ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር በተተከሉ ችግኞች ውጤት ተገኝቷል።

በዚህም መሠረት ዘንድሮ በችግኝ ለመሸፈን ከታቀደው መሬት በ50 በመቶው በላይ ለምግብነት የሚውሉ ችግኞች እንደሚተከሉ ገልጸው፤ አጠቃላይ የዝግጅት ተግባራቱም 92 በመቶ መድረሱን አስታውቀዋል።

በክልሉ ዘንድሮ ለአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር ከ1 ሚሊየን ሔክታር በላይ አዲስ መሬት መዘጋጀቱንም አረጋግጠዋል።

ከዚህ ውስጥም ለደን የሚያገለግሉ ችግኞች ከ400 ሺህ ሔክታር በሚልቅ መሬት ላይ በኩታ ገጠም እንደሚተከሉ አስረድተዋል።

የሚተከሉ ችግኞች የመሬት ለምነትን የሚመልሱ፣ ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ፣ ከሚለማው ሰብል ጋር የሚስማሙና አርሶ አደሩ በውስን መሬት ላይ ሁለገብ ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል።
 
በመንግሥት፣ በኢንተርፕራይዞች፣ በማኅበራትና በአርሶ አደሮች አማካኝነት፤ በ1 ሺህ 200 የችግኝ ጣቢያዎች ችግኝ እየተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።
 
አሁን ላይ የዝናብ እጥረት ያለባቸው አካባቢዎች እርጥበትን በመቆጠብ ውኃን ይዘው ማቆየት የሚችሉ የችግኝ ጉድጓዶች እየተዘጋጁ መሆኑንም አመላክተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም