ቀጥታ፡

የግብርና ምርምር ተቋማት በመደመር እሳቤ ቅንጅታቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 6/2018 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ የግብርና የምርምር ተቋማት በመደመር እሳቤ ያላቸውን ትስስርና ቅንጅት ሊያጠናክሩ እንደሚገባ  የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን (ዶ/ር)  ገለፁ።

የግብርና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት እና ከኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ጋር በመተባበር የተዘጋጀ በብሔራዊ የግብርና ምርምር ሥርዓቶች ላይ ያተኮረ ውይይት ተካሄዷል።


 

ውይይቱ "በኢትዮጵያ ብሔራዊ የግብርና ምርምር ሥርዓቶችን እንደገና ማጤን፤ተቋማዊ ውህደት፣ ስትራቴጂካዊ ቅንጅት እና የውጤታማነት መንገዶች" በሚል መሪ ሃሳብ ተካሄዷል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ ባለፉት አሥርት ዓመታት በግብርና ዘርፍ ለምርምር ስራዎች በሰፊ ኢንቨስት ተደርጓል። 

የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት፣ የክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩቶች፣ ዩኒቨርሲቲዎች እና ዓለም አቀፍ የምርምር አጋሮች እውቀትን፣ ቴክኖሎጂን እና ፈጠራን በማመንጨት ረገድ ወሳኝ ሚና መጫወታቸውን ጠቅሰዋል።

እነዚህ ጥረቶች ለምርታማነት እድገት፣ ለቴክኖሎጂ እና ለአቅም ግንባታ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ የምርምር ሥርዓቱ ሙሉ አቅሙን እንዳይጠቀም ተቋማዊ መበታተን፣ ደካማ ቅንጅት እና የምርምር ውጤቶች ወደ ተግባር ተቀይረው አርሶ አደሩ ዘንድ የመድረስ ውስንነት ተግዳሮቶች እንዳሉ ጠቁመዋል።

ይህን ለማቃለል የምርምር ሥርዓቱ በመደመር ዕሳቤ ሊቃኝ እንደሚገባ ተናግረው፤ ተቋማት በተናጠል ከመሥራት ይልቅ በቅንጅት እንዲሠሩ፣ ሳይንስ ከፖሊሲ ጋር እንዲተሳሰር እና በምርምር የሚገኘው ዕውቀት በአርሶ አደሩ ሕይወት ላይ ለውጥ ማምጣት እንደሚያስችል ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ዋና ስራ አስፈፃሚ  ፕሮፌሰር ተከተል ዮሐንስ በበኩላቸው፤ አካዳሚው በስድስት ዋና ዋና የሥራ ዘርፎች ተከፋፍሎ ተግባራቱን እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።


 

አካዳሚው በብቃትና በላቀ የሙያ ተሳትፎ ላይ የተመሰረተ ማህበር እንደመሆኑ የግብርና የሥራ ቡድን ከ70 በላይ አባላትን በመያዝ ከአካዳሚው ግዙፍና ቀዳሚው የሥራ ዘርፍ እንደሆነ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ንጉሤ ደቻሳ በበኩላቸው እንዳሉት፤ የግብርና ምርምር ስራዎች ውጤታማና ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸው እንዲሆኑ የተቀናጀ አሰራርና ብሔራዊ ስትራቴጂ መቅረጽ አስፈላጊ ነው።


 

የግብርና ልማቱን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ስልታዊ ለሆኑ ጉዳዮች ቅድሚያ የሚሰጥ የጋራ መመሪያ መኖር እንዳለበትም አመልክተዋል።

የቢሾፍቱ ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ታምራት ደገፋ (ዶ/ር)፤ በምርምር ተቋማት መካከል አዲስ ተቋማዊ ውህደትና የአፈጻጸም መለኪያ አስፈላጊነትን አንስተዋል።


 

የምርምር ሥራችንም ሆነ ግባችንን በማሳካት ረገድ ስኬታማ መሆን አለመሆናችንን የምንለካባቸው ቁልፍ የአፈጻጸም አመልካቾች  መዘጋጀት አለባቸው ሲሉ ተናግረዋል።

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ምሁር ፕሮፌሰር ፍሬው መክበብ  እንደተናገሩት፤ ዘርፉን በአግባቡ መምራት የሚያስችል  የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት ይገባል።


 

ይህ ብሔራዊ ምርምርን በብቃት መምራት እንደሚያስችል ገልጸው፤ ለዘርፉ አስፈላጊውን በጀት መመደብ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የዓለም አቀፍ የግብርና ምርምር አማካሪ ቡድን የአፍሪካ ግንኙነት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ናበሙኮሎ ኮቪክ (ዶ/ር) በግብርና ዘርፍ ያሉ የምርምር ተቋማት በተወሰኑ ዘርፎች ላይ በሚያተኩሩ የልህቀት ማዕከላት እንዲደራጁ ሐሳብ አቅርበዋል። 


 

የዘርፉን ውጤታማነት ይበልጥ ለማረጋገጥ የሚደረገው ቅንጅት በበቂ በጀት ሊደገፍ እንደሚገባም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም