ቀጥታ፡

የግብርናው ዘርፍ ምርታማነት የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚያስችል አቅም እየፈጠረ ነው

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 6/2018(ኢዜአ)፡-ከሀገራዊ ለውጡ ማግስት በግብርናው ዘርፍ የተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች የምርታማነት አቅምን በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ የኢትዮጵያን የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ የሚያስችል አቅም እየፈጠረ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) ገለጹ።

በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና በግብርና ሚኒስቴር ትብብር "ከተረጅነት ወደ ምርታማነት" በሚል መሪ ሃሳብ በአዳማ ከተማ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።


 

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር)፥ የለውጡ መንግሥት በብዝኅ የኢኮኖሚ ሥርዓት የግብርና ምርታማነትን የሚያሻሽሉ የፖሊሲ እርምጃዎች ተወስደዋል ብለዋል።

በዚህም በአጭር ጊዜ ውስጥ በሁሉም መስክ የተኪ ምርት አቅምን በማሳደግ የወጪ ንግድ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ማሳደጉን ጠቅሰዋል።

የግብርና ዘርፍ በዝናብ ጥገኝነት ላይ የተንጠለጠለና የዜጎችን የምግብ ሉዓላዊነት ፈታኝ አድርጎት ቆይቶ እንደነበር አስታውሰዋል።


 

የአየር ንብረት ለውጥና የአካባቢ ደህንነት መመናመንም በተለያዩ ወረዳዎች ላይ የሚኖሩ ዜጎች የእርዳታ ጥገኛ ሆነው እንደቆዩ አስረድተዋል።

በአጭር ጊዜ ተግባራዊ የተደረጉ የፖሊሲ እርምጃዎችና የሴፍቲኔት ልማታዊ መርሃ ግብር በርካታ ዜጎችን የግብርና ምርታማነት በማሳደግ ከተረጅነት ወደ ምርታማነት ማሸጋገር እንደተቻለ አብራርተዋል።

በዚህም በሁሉም የግብርና መስክ የተፈጠረው የምርታማነት አቅም የኢትዮጵያን የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ የሚያስችል አቅም እየተፈጠረ መሆኑን አንስተዋል።


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሰይፈ ደርቤ በበኩላቸው፥ መገናኛ ብዙኅን በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና በተለያዩ የልማት ስራዎች ላይ ወሳኝ አጀንዳ በመቅረፅ ሰፊ ስራ እየሰሩ ነው ብለዋል።

ኢዜአም የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን የተረጅነት ታሪክን በማስቀረት የምግብ ሉዓላዊነት በማረጋገጥ የዜጎችን ክብር የሚያጎናጽፍ ድል እየተመዘገበ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር "የግብርና ምርታማነት ለምግብ ሉዓላዊነትና ለሀገራዊ ክብር" በሚል መሪ ሀሳብ በለውጡ ዓመታት በግብርናው ዘርፍ የተገኙ ውጤቶች ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ መጋቢት 23 ቀን 2018 ዓም ማካሄዱ ይታወቃል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም