"ከተረጅነት ወደ ምርታማነት" በሚል መሪ ሃሳብ በአዳማ ከተማ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ይገኛል - ኢዜአ አማርኛ
"ከተረጅነት ወደ ምርታማነት" በሚል መሪ ሃሳብ በአዳማ ከተማ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ይገኛል
አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 6/2018(ኢዜአ)፡-በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና በግብርና ሚኒስቴር ትብብር "ከተረጅነት ወደ ምርታማነት" በሚል መሪ ሃሳብ በአዳማ ከተማ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እውነቴ አለነ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሰማ ጥሩነህ (ዶ/ር)፣ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) እና የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) ተገኝተዋል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሰይፈ ደርቤ፣ የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ጌቱ ገመቹ ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የፌደራልና የክልል ግብርና ቢሮ የሥራ ኃላፊዎችና የግብርና ሙያተኞች ተገኝተዋል።
በመድረኩም የኢትዮጵያን የግብርና ምርታማነት በማስቀጠል የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ የመነሻ ሃሳቦች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።
ኢትዮጵያ በበጋ መስኖ ስንዴ፣ በመኸርና በበልግ ወራት የሰብል ምርታማነት፣በሌማት ትሩፋት እና በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚያስችል እመርታዊ ውጤት በማስመዝገብ ላይ ትገኛለች።
ለአብነትም የዘመናት ተረጅነትን በማስቀረት ከራስ አልፎ ስንዴን ወደ ውጪ በመላክ ወደተሟላ ሀገራዊ ክብር መሸጋገር የሚያስችል የታሪክ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች።