የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ27ኛ ሳምንት የጨዋታ መርሐ ግብር ላይ ማሻሻያ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ27ኛ ሳምንት የጨዋታ መርሐ ግብር ላይ ማሻሻያ ተደረገ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 6/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ27ኛ ሳምንት የጨዋታ መርሐ ግብር ላይ መጠነኛ ማሻሻያ መደረጉን የሊጉ አክሲዮን ማህበር አስታወቀ።
ፕሪሚየር ሊጉ ከ25ኛ ሳምንት ጀምሮ በአዲስ አበባ እና በሃዋሳ ከተሞች በድምቀት እየተካሄደ እንደሚገኝ ይታወቃል።
ይሁን እንጂ የ27ኛ ሳምንት የመጀመርያ ቀን ሁለተኛ ጨዋታ የነበረው የሃዋሳ ከተማ እና ምድረ ገነት ሽሬ ግጥሚያ፣ በሃዋሳ ከተማ ባጋጠመ አስቸጋሪ የአየር ሁኔታ ምክንያት ሜዳው ለጨዋታ አመቺ ባለመሆኑ ሳይከናወን ቀርቷል።
ይህንን ተከትሎ የውድድርና ስነ ስርዓት ኮሚቴ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ፣ ሳይከናወን የቀረው የሃዋሳ ከተማ እና ምድረ ገነት ሽሬ ጨዋታ ረቡዕ ሚያዝያ 7 ቀን 2018 ዓ.ም ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ እንዲደረግ ወስኗል።
በተጨማሪም በዚሁ ዕለት ሊካሄድ የነበረው የድሬዳዋ ከተማ እና መቻል ጨዋታ ወደ ምሽቱ 12 ሰዓት ተገፍቶ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም እንዲከናወን መርሐ ግብሩ ተሻሽሏል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ሚያዝያ 6 እና 7 ሊካሄዱ የታቀዱ የ27ኛ ሳምንት ጨዋታዎች፣ ተመሳሳይ የአየር ሁኔታ አጋጥሞ መጫወት ካልተቻለ ጨዋታዎቹ በቀጣዩ ቀን በተለዋጭ ሜዳ እና ሰዓት እንደሚከናወኑ የውድድርና ስነ ስርዓት ኮሚቴው አስታውቋል።
አክሲዮን ማህበሩ ባስተላለፈው መረጃ መሠረት፤ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የሚደረጉ ቀሪ የሳምንቱ ጨዋታዎች የቀረፃ ሽፋን ብቻ የሚሰጣቸው ሲሆን የቀጥታ ስርጭት ግን አይኖራቸውም።