በምስራቅ ቦረና ዞን በበልግ አዝመራ ከ160 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ተሸፍኗል - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ቦረና ዞን በበልግ አዝመራ ከ160 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ተሸፍኗል
ነገሌ ቦረና፤ሚያዝያ 6/ 2018 (ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ቦረና ዞን ቆላማ ወረዳዎች በዘንድሮው የበልግ አዝመራ ከ160 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት ገለጸ።
ምስራቅ ቦረና ቆላማና ዝናብ አጠር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በብዛት የእንስሳት እርባታ የሚካሄድበት ቢሆንም፤ከመጋቢት 15 እስከ ሚያዝያ አጋማሽ ያለው ጊዜ ዋነኛው የበልግ ዝናብና የእርሻ ወቅት መሆኑ ተገልጿል።
በጽሕፈት ቤቱ የሰብል ልማትና ጥበቃ ባለሙያ አቶ ቦነያ ሁቃ እንደገለጹት፤ በዘንድሮው የበልግ ወቅት 176 ሺህ 223 ሄክታር መሬት ታርሶ ለዘር ተዘጋጅቷል።
በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች ለበልግ አዝመራ ከተዘጋጀው መሬት ውስጥ እስካሁን 160 ሺህ 539 ሄክታር የሚሆነው በአራት ዋና ዋና ሰብሎች መልማቱን ገልጸዋል።
በቆላማ ወረዳዎቹ የታረሰው መሬት በስንዴ፣ በጤፍ፣ በበቆሎና በቦለቄ ምርጥ ዘር እየለማ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በዚህ የበልግ አዝመራ 137 ሺህ 324 አርሶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች በመሳተፍ ላይ ሲሆኑ፤ ከእነዚህም መካከል 20 ሺህ 297 ያህሉ ሴቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።
በዞኑ በበልግ አዝመራ ከሚለማው መሬት በአጠቃላይ ከ3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል ብለዋል።