የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 6/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 27ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ አራት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።
ከቀኑ 9 ሰዓት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሲዳማ ቡና በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሊጉ ባደረጋቸው 26 ጨዋታዎች መካከል ስምንቱን ሲያሸንፍ በተመሳሳይ ስምንት ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። በ10 ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። በ26ቱ ጨዋታዎች ላይ 35 ጎሎችን ሲያስቆጥር 32 ጎሎች ተቆጥረውበታል።
ቡድኑ በ34 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው ሲዳማ ቡና 26 ጨዋታዎችን አከናውኖ በ13ቱ አሸንፎ በአራቱ ተሸንፎ ዘጠኝ ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል።
በ26ኛ ሳምንት መቀሌ 70 እንደርታን 3 ለ 0 ያሸነፈው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ይጫወታል።
በአንጻሩ በ26ኛ ሳምንት በመቻል የ3 ለ 1 ሽንፈት ያስተናገደው ሲዳማ ቡና ማሸነፍ ከሽንፈቱ በማገገም የሊጉን መሪነት ለማጠናከር ያስችለዋል።
ጨዋታው ተመጣጣኝ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።
በሌላኛው መርሐ-ግብር ወላይታ ድቻ ከፋሲል ከነማ ምሽት 12 ሰዓት ላይ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ወላይታ ድቻ በውድድር ዓመቱ 26 ጨዋታዎችን አድርጎ ስድስቱን ሲያሸንፍ በሰባቱ ሽንፈት አስተናግዷል። 13 ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።
27 ግቦችን በ26ቱ ጨዋታዎች ላይ ሲያስቆጥር 26 ጎሎችን አስተናግዷል። ቡድኑ በ31 ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በሊጉ ካከናወናቸው 26 ጨዋታዎች መካከል ዘጠኙን ያሸነፈው ፋሲል ከነማ በበኩሉ አምስት ጊዜ ተሸንፏል። 12 ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል። 18 ግቦችን ሲያገባ 15 ጎሎች ተቆጥረውበታል።
ፋሲል ከነማ በ39 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዟል።
በ26ኛ ሳምንት ወላይታ ድቻ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲን፣ ፋሲል ከነማ ሃዋሳ ከተማን 1 ለ 0 አሸንፈዋል።
ሁለቱም ቡድኖች ተከታታይ ድላቸውን ለማስመዝገብ ይፋለማሉ።
ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ አዳማ ከተማ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይጫወታሉ።
አዳማ ከተማ በ33 ነጥብ 10ኛ ደረጃን ይዟል። ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ38 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ባለፉት ስድስት የሊግ ጨዋታዎች ያላሸነፈው አዳማ ከተማ ወደ ድል መንገድ ለመመለስ ይጫወታል።
ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ድል ያልቀናው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሶስት ነጥብ ለማግኘት ይፋለማል።
ሀድያ ሆሳዕና ከኢትዮጵያ ቡና ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ሀድያ ሆሳዕና በ32 ነጥብ 13ኛ ደረጃን ይዟል። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ኢትዮጵያ ቡና በበኩሉ በ36 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
በ26ኛ ሳምንት አርባምንጭ ከተማን 1 ለ 0 ያሸነፈው ሀድያ ሆሳዕና ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ይፋለማል።
በአንጻሩ በ26ኛ ሳምንት ከሸገር ከተማ አንድ አቻ የተለያየው ኢትዮጵያ ቡና ማሸነፍ ወደ ድል መንገድ ይመልሰዋል።