ቀጥታ፡

የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍጻሜ የመልስ ጨዋታዎች 

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 6/2018 (ኢዜአ):- በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዛሬ ሁለት የሩብ ፍጻሜ የመልስ ጨዋታዎች ይካሄዳሉ። 

ምሽት አራት ሰዓት ላይ ሊቨርፑል ፒኤስጂን በአንፊልድ ሮድ ስታዲየም ያስተናግዳል።


 

ሁለቱ ቡድኖች ባለፈው ሳምንት ባደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ ፒኤስጂ በዴዚሬ ዱዌ እና ክቪቻ ክቫራትስኬሊያ ጎሎች 2 ለ 0 አሸንፏል።

ውጤቱን ተከትሎ የወቅቱ የውድድሩ አሸናፊ ፒኤስጂ ወደ ግማሽ ፍጻሜ የመግባት እድሉን አስፍቷል።

የስድስት ጊዜ የሊጉ አሸናፊ ሊቨርፑል ውጤቱን የመቀልበስ ጠንካራ ፈተና ይጠብቀዋል።

ሁለቱ ቡድኖች ባለፈው የውድድር ዓመት በጥሎ ማለፉ ተገናኝተው ፒኤስጂ በድምር ውጤት በማሸነፍ ሩብ ፍጻሜ መግባቱ የሚታወስ ነው። 


 

ሌላኛው ጨዋታ ምሽት አራት ሰዓት ላይ አትሌቲኮ ማድሪድ እና ባርሴሎናን በዋንዳ ሜትሮፖሊታኖ ስታዲየም ያገናኛል። 

የስፔን ክለቦቹ በመጀመሪያው ዙር በካምፕ ኑ ስታዲየም ባከናወኑት ጨዋታ አትሌቲኮ ማድሪድ 2 ለ 0 አሸንፏል።

ሁሊያን አልቫሬዝ እና አሌክሳንደር ሶርሎዝ ግቦቹን አስቆጥረዋል። የማድሪዱ ክለብ ከሜዳው ውጪ ያገኘው ድል ወደ ግማሽ ፍጻሜ የመግባት እድሉን አስፍቶታል።

ባርሴሎና ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ በዘንድሮው የውድድር ዓመት በሜዳው ለማሸነፍ ከባድ የሆነው አትሌቲኮ ማድሪድን ከሁለት ጎል በላይ ልዩነት ማሸነፍ ይጠበቅበታል

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም