ቀጥታ፡

በሐረሪ ክልል 250 አባወራዎችን ያካተተ ሞዴል መንደር ሊገነባ ነው

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 5/2018 (ኢዜአ)፡- በሐረሪ ክልል በገጠር ኮሪደር ልማት በቀጣይ ሁለት ወራት 250 አባዎራዎችንና እማወራዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሞዴል መንደር እንደሚገነባ የክልሉ ርዕሰ መሥተዳድር ኦርዲን በድሪ አስታወቁ።

በክልሉ የገጠር ኮሪደር ዐቢይ ኮሚቴ ዕቅድ እና አፈጻጸም ላይ ውይይት ተካሂዷል።

በዚሁ ወቅት ርዕሰ መሥተዳድሩ እንዳሉት፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሐሳብ አመንጪነት የተጀመረው የኮሪደር ልማት ከፅዱና ውብ አካባቢ ባለፈ ለዜጎች ምቹ የመኖሪያ ሥፍራ እንዲፈጠር እያስቻለ ነው።


 

በዚህም መሠረት በሐረር ከተማ በኮሪደር ልማት ዘርፍ የተመዘገበውን ውጤት በገጠሩ ክፍል ለማስፋት እየተሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

በገጠር አካባቢ የሚከናወኑ የኮሪደር ልማት ሥራዎችም፤ የአርሶ አደሩን የአኗኗር ሁኔታ ለመቀየር የሚያስችሉ መሆናቸውን ነው ያመላከቱት።

ለአብነትም አርሶ አደሩ ያለውን ሀብትና ፀጋ በአግባቡ ተጠቅሞ ኢኮኖሚውን በማሳደግ በዚያው ልክ የተመቸ ኑሮ እንዲመራ የሚያግዝ መሆኑን ነው ያስረዱት።

በክልሉ የሞዴል ገጠር መንደር መፈጠሩን የገለጹት ርዕሰ መሥተዳድሩ፤ ሞዴል መንደሩም ውኃና የኃይል አቅርቦትን ጨምሮ ሌሎች መሠረተ-ልማቶች እንዲሟሉ ተደርጓል ብለዋል።

በቀጣይ ሁለት ወራትም 250 አባዎራዎችንና እማወራዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሞዴል የአርሶ አደሮች የመኖሪያ መንደር ለመገንባት ይሠራል ነው ያሉት።

የገጠር ኮሪደር ልማት ሥራ በላቀ ቁርጠኝነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠው፤ ለዚህም አርሶ አደሩ እያከናወነው የሚገኘውን የላቀ ተሳትፎና ድጋፍ እንዲያጠናክር አሳስበዋል።

በየደረጃው የሚገኘው አመራርም ሥራዎችን በቅንጅት እና በትብብር እንዲሠራ ነው ያሳሰቡት።

#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ #የገጠር_ኮሪደር

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም