ቀጥታ፡

መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎችን የፈጠራ ክህሎት ማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ ነው

ሮቤ፣ ሚያዝያ 5/2018 (ኢዜአ)፦ የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂና የፈጠራ ዝንባሌ ያላቸው ተማሪዎችን ለተሻለ ውጤት ማብቃት የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ።

ዩኒቨርሲቲው ከስቴም (STEM) ማዕከል ጋር በመተባበር ባዘጋጀው አውደ ርዕይ ላይ፣ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢንጂነሪንግ እና ሒሳብ ዘርፎች ሥልጠና የወሰዱ የሮቤ ከተማ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የፈጠራ ሥራዎቻቸውንና ግኝቶቻቸውን በማቅረብ ላይ ይገኛሉ።  


 

በመርሐግብሩ ላይ የተገኙት የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዚዳንት ረዳት ፕሮፌሰር ኢሳ ሐሰን እንደገለጹት፤ ተቋሙ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ፍላጎትና ችግር መሠረት ያደረጉ ምርምሮችንና አገልግሎቶችን እያከናወነ ይገኛል።   


 

ዩኒቨርሲቲው ከ"ስቴም ፓዎር" (STEMpower) ድርጅት ጋር በመተባበር ያቋቋመው ቤተ-ሙከራ፣ በዘርፉ የሚታዩ ተግዳሮቶችን በመፍታት ረገድ ትልቅ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልጸዋል።   

ቤተ-ሙከራው ተማሪዎች በንድፈ-ሀሳብ የተማሩትን በተግባር እንዲለማመዱ በማድረግ፣ ሀገራዊና አካባቢያዊ ችግሮችን የሚፈታ ትውልድ ለመቅረጽ እያገዘ መሆኑን ጠቅሰዋል።   

የሮቤ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ጀማል አባገሮ በበኩላቸው፣ አውደ ርዕዩ ተተኪው ትውልድ የፈጠራ አቅሙን እንዲያጎለብት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል።   


 

የስቴም ፓዎር ኢትዮጵያ የኦፕሬሽን ማኔጀር አቶ አንተነህ ፍሰሃ በ"ዲጂታል ኢትዮጵያ" ስትራቴጂ አማካኝነት በሀገር ደረጃ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ አበረታች ለውጦች እየታዩ መሆኑን ገልጸዋል።   

ይህ አውደ ርዕይ የተማሪዎችን ዝንባሌ ከማሳደግ ባለፈ፣ ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስኬት ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረውም አክለዋል።   


 

በአውደ ርዕዩ ላይ የተሳተፉ ተማሪዎች በአካባቢያቸው የሚገኙ ቁሳቁሶችን በመጠቀም፣ ለችግር ፈቺ የሆኑ የቴክኖሎጂ ዲዛይኖችን አቅርበዋል።   

ተማሪዎቹ እንዲህ ያሉ መድረኮች ክህሎታቸውን ለማሳደግና ለወደፊት የፈጠራ ሥራዎቻቸው መነሳሳትን እንደሚፈጥሩላቸው ገልጸዋል።

የሳይንስና ቴክኖሎጂ አውደ ርዕይ ነገም ቀጥሎ እንደሚውል ታውቋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም