በነፃ የንግድ ቀጣናዎች ለተሰማሩ ባለሀብቶች የገቢ ግብር ዕፎይታ ተፈቀደ - ኢዜአ አማርኛ
በነፃ የንግድ ቀጣናዎች ለተሰማሩ ባለሀብቶች የገቢ ግብር ዕፎይታ ተፈቀደ
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 5/2018 (ኢዜአ)፦ በነፃ የንግድ ቀጣናዎች ውስጥ ግብዓትና ምርት ለገበያ የሚያቀርቡ ባለሀብቶች ከገቢ ግብር ነፃ እንዲሆኑ በገንዘብ ሚኒስቴር ውሳኔ ተላለፈ።
ሚኒስቴሩ ይህንን የፈቀደው የንግድ ቀጠናዎቹ ባለሀብቶችን ይበልጥ የሚስቡ እንዲሆኑ ለማድረግ መሆኑን ገልጿል።
የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ልማት በሚፈለገው መጠን እንዳያድግ ምክንያት ከሆኑት መካከል የካፒታል እጥረት፣ የግብዓት አቅርቦት ችግር እና የባለሙያ እጥረት በዋነኛነት የሚጠቀሱ መሆናቸውን ሚኒስቴሩ በመረጃው ጠቁሟል።
በመሆኑም እነዚህን ችግሮች ደረጃ በደረጃ በማቃለል የአገር ውስጥ ኢንዱስትሪ ልማትን ማሳደግ እንደሚገባ አስታውቋል።
በዚህም መሠረት ግብዓቶች እና ሌሎችም ምርቶች በበቂ መጠን ለገበያ እንዲቀርቡ ለማድረግ፣ አስመጪዎች ምርቱን ለገበያ ከማቅረባቸው በፊት የሚከፍሉት ቀረጥ እና ታክስ ውስን በሆነው ካፒታላቸው ላይ የሚያሳድረውን ጫና ማቃለል አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።
በነዚህ ምክንያቶች አስመጪዎች ግብዓቶችን እና ምርቶችን ቀረጥና ታክስ ሳይከፍሉ ወደ አገር አስገብተው፣ ለግብዓቱ ወይም ለምርቱ ገበያ ባገኙ ጊዜ ቀረጥና ታክሱን የሚከፍሉበትን አሰራር የሚፈቅድ የነፃ የንግድ ቀጣና አሰራር ተዘርግቷል።
ይህንን ሥርዓት የሚያስፈጸሙ ነፃ የንግድ ቀጣናዎችም በየአካባቢው የተቋቋሙ መሆኑ ተመልክቷል።
ይህንን ተከትሎም በነፃ የንግድ ቀጣናዎች ውስጥ ተሰማርተው ምርትና ግብዓት ለገበያ የሚያቀርቡ ባለሀብቶች ከላይ ከተጠቀሰው የታክስ አከፋፈል ስርዓት በተጨማሪ ከገቢ ግብር ነፃ እንዲሆኑ ተደርጓል።
በመሆኑም ባለሀብቶች ይህንን ዕድል በመጠቀም በነፃ የንግድ ቀጣናዎች ውስጥ እንዲሰማሩ የገንዘብ ሚኒስቴር ጥሪውን አስተላልፏል።