ቀጥታ፡

በምዕራብ ሸዋ ዞን ለ2018/19 የምርት ዘመን የግብርና ግብዓቶች እየቀረቡ ነው

አምቦ፤ ሚያዝያ 5/2018 (ኢዜአ)፡-በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን የ2018/19 ምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ የማቅረብ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የዞኑ የኅብረት ሥራ ማህበራት ኤጀንሲ አስታወቀ።

የኤጀንሲው ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ መሰረት በላይ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በምርት ዘመኑ የታቀደውን የሰብል ልማት ግብ ለማሳካት የተለያዩ የግብርና ግብዓቶች ከወዲሁ ለአርሶ አደሩ እየተሰራጩ ይገኛሉ።


 

በምርት ዘመኑ ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለማሰራጨት ታቅዶ እየተሠራ ሲሆን፤ እስካሁን ከ461 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ በየወረዳው ለሚገኙ መሠረታዊ የኅብረት ሥራ ማህበራት ደርሷል ብለዋል።

የማዳበሪያ አቅርቦቱ ለአርሶ አደሩ በዲጂታል አገልግሎት እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይኸም ለፍትሐዊ ስርጭቱ እንደሚያግዝ አስታውቀዋል። 

በተመሳሳይ 8 ሺህ 244 ኩንታል ምርጥ ዘር ለማሰራጨት ታቅዶ፣ እስካሁን ከ2 ሺህ ኩንታል በላይ የበቆሎ ምርጥ ዘር ቀርቧል ነው ያሉት።

ይህ የግብዓት ስርጭት በዋናነት በአምቦ እና በቦረባኮ የገበሬዎች ዩኒየን በኩል እየተከናወነ ሲሆን፤ ቀሪዎቹ ግብዓቶችም በተጠናከረ ሁኔታ እንደሚቀርቡ አስታውቀዋል። 

ይህ ዝግጅት በዞኑ በመስኖና በመኸር የሚካሄደውን የሰብል ምርታማነት ለማሳደግ ያለመ መሆኑንም አክለዋል።

አርሶ አደሩ የምግብ ዋስትናውን ከማረጋገጥ ባለፈ፣ የኢኮኖሚ አቅሙን እንዲያሳድግና ለአካባቢው ሥነ-ምህዳር ተስማሚ የሆኑ ሰብሎችን እንዲያመርት አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ወይዘሮ መሰረት ገልጸዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የዞኑ አርሶ አደሮች ግብዓቶቹ በወቅቱ መድረሳቸው ለሥራቸው መሳካት ትልቅ እገዛ ማድረጉን ገልጸዋል። 


 

አርሶ አደር ሀጫሉ ባይሳ፤ "በመጪው መኸር በቆሎና ሌሎች ሰብሎችን ለማልማት የሚያስፈልገንን ግብዓት አግኝተናል፤ አሁን ላይ መሬታችንን ደጋግመን በማረስ ለዘር ዝግጁ እያደረግን ነው" ብለዋል።

ሌላው አርሶ አደር ወልደሰማያት ለታ፤ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር በወቅቱ መድረሱ የእርሻ ሥራቸውን በጊዜ ለማቀላጠፍ እንደረዳቸው ጠቅሰው፣ በአምስት ሄክታር መሬታቸው ላይ በቆሎና ጥራጥሬ ለማልማት ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ከዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በ2018/19 ምርት ዘመን በምዕራብ ሸዋ ዞን ከ900 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ይለማል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም