ኢትዮጵያ የ89ኛውን ዓለም አቀፍ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ጉባኤን እንድታስተናግድ ተመረጠች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የ89ኛውን ዓለም አቀፍ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ጉባኤን እንድታስተናግድ ተመረጠች
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 5/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የ89ኛውን ዓለም አቀፍ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር (AIPS) ጉባኤን እንድታስተናግድ ተመርጣለች።
መንግስት ለስፖርት ዘርፍ በሰጠው ልዩ ትኩረት እና እየገነባ ባለው መሰረተ ልማት ስፖርታዊ ሁነቶችና ኮንፈረንሶች ወደ ኢትዮጵያ እየመጡ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ገልጿል።
በሉዛን ስዊዘርላንድ በተካሄደው 88ኛው ዓለም አቀፍ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር (AIPS) ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ በ2027 (በ2019 ዓ.ም) የሚካሄደውን 89ኛውን ጉባኤ በይፋ እንድታስተናግድ ተመርጣለች።
ይህ ታላቅ ስኬት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ኩራት ከመሆኑም በላይ፣ ለኢትዮጵያ ተጨማሪ እድልንም ይዞ የሚመጣ መሆኑን ሚኒስቴሩ አመልክቷል።
ይህ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነው ጉባኤ፣ በኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ባደረገው ስልታዊ ጥረት እና መንግስት በሰጠው ድጋፍ የተገኘ ትልቅ ውጤት መሆኑን ገልጿል።
ኢትዮጵያ ይህን ዓለም አቀፍ ጉባኤ ለማስተናገድ መመረጧ የሀገሪቷን የዲፕሎማሲያዊ ብቃትና የሚዲያ ማዕከልነት በዓለም አቀፍ መድረክ ዳግም የሚያረጋግጥ መሆኑ ተመላክቷል።
በተለይም መንግሥት በየደረጃው ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ስታዲየሞችንና ሁለንተናዊ የስፖርት መሠረተ ልማቶችን ለመገንባት እያከናወነ ያለውን ተግባርና ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት ለዓለም ማህበረሰብ ለማሳየት ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥርም ተገልጿል።
በመቶዎች የሚቆጠሩ ተደማጭነት ያላቸውን የዓለም ስፖርት ጋዜጠኞች በአዲስ አበባ መስተናገዳቸው፤ በስፖርቱ ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶችን ለማስተዋወቅ፣ የኢትዮጵያን የቱሪዝም ሀብት የበለጠ ለመግለጥ እንዲሁም ለሀገር ውስጥ ባለሙያዎች ሰፊ የልምድ ልውውጥ ለመፍጠር ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል።
ይህም መንግሥት ስፖርቱን የሰላምና የልማት ምሰሶ ለማድረግ ለሚሠራው ሥራ ተጨማሪ አቅምና ዓለም አቀፍ ዕውቅና የሚሰጥ መሆኑን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
ኢትዮጵያ ጉባኤውን እንድታስተናገድ ወሳኝ ሚና ለተጫወተው የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ሚኒስቴሩ ምስጋና አቅርቧል።