ቀጥታ፡

በዞኑ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሚተከሉ ከ142 ሚሊዮን በላይ ችግኞች እየተዘጋጁ ነው

ጎንደር፤ ሚያዚያ 5/2018 (ኢዜአ)፦በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በክረምት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሚተከሉ ከ142 ሚሊዮን በላይ ሀገር በቀል ችግኞች የማዘጋጀት ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡

የመምሪያው ሃላፊ አቶ ንጉሴ ማለደ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዞኑ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን አጠናክሮ በማስቀጠል የአካባቢውን ምርታማነት ለማሳደግ እየተሰራ ነው።


 

ለዚህም በዞኑ ሥር ባሉ የተለያዩ ወረዳዎች በተቋቋሙ 12ሺህ የችግኝ ጣቢያዎች ከ142 ሚሊዮን በላይ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውና የአካባቢውን ስነ ምህዳር ለመጠበቅ የሚያግዙ ችግኞች እየፈሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።  

ችግኞቹ በመጪው ክረምት በአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር የሚተከሉ መሆናቸውን ገልጸው፣ እስካሁን በተደረገ ጥረትም ቀድመው የሚፈሉ 76 ሚሊዮን ሀገር በቀል ችግኞችን በማፍላት የእንክብካቤ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


 

በክረምቱ ከሚተከሉ ችግኞች ውስጥ ከ40 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የሚሰጡ አቮካዶ፣ ማንጎ፣ ቡናና መሰል የፍራፍሬ ችግኞች እንደሆኑም አስረድተዋል።

እንደ አቶ ንጉሴ ገለጻ፣ በመጪው ክረምት 33ሺህ ሄክታር የሚሸፍን የችግኝ ተከላ ሥራ ለማከናወን የቦታ መረጣና ሌሎች ዝግጅቶች እየተደረጉ ይገኛሉ።፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአካባቢን ስነ ምህዳር ከማስጠበቅ ባለፈ በርካታ ወጣቶች በግላቸው ችግኝ አፍልተው በመሸጥ የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩንም አያይዘው ገልጸዋል።


 

የዞኑ ህብረተሰብ ችግኝ የተተከለባቸውን ቦታዎች ከመከለል ባለፈ በራሱ ወጪ ሠራተኞችን ቀጥሮ የእንክብካቤና የጥበቃ ሥራ እያከናወነ መሆኑን ገልጸው፣ ባለፈው ዓመት ክረምት ከተተከሉ 121 ሚሊዮን በላይ ችግኞች 86 በመቶው ጸድቀዋል ብለዋል።

የደን ልማት ሥራ ለግብርና ሥራችን መሰረት በመሆኑ በየዓመቱ በክረምት ወራት ችግኝ በመትከልና በመንከባከብ ተሳትፎ እያደረጉ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የወገራ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር በላይነህ ስጦታው ናቸው፡፡ 

የጎንደር ዙሪያ ወረዳ ነዋሪ ወጣት አምሳሉ ገነቱ በበኩሉ እንዳለው እሱና ጓደኞቹ በማህበር ተደራጅተው ባቋቋሙት የችግኝ ጣቢያ ሀገር በቀል የዛፍና የፍራፍሬ ችግኞችን አፍልተው ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ እየሆኑ መጥተዋል፡፡


 

ለመጪው ክረምትም ከ500 ሺህ በላይ ችግኞች በማፍላት ለገበያ ለማቅረብ እየተዘጋጁ መሆኑን ጠቁመው፣ ከችግኞቹ መካከል ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው የአቮካዶ እና የማንጎ ዝርያዎች ይገኙበታል ብለዋል።

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አሁናዊ የደን ሽፋን መጠን 15 ነጥብ 2 በመቶ መድረሱን ከዞኑ ግብርና መምሪያ የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም