ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነትን ማብሰር የሚያስችሉ ተጨባጭ ተግባራትን እያከናወነች ነው

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 5/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም በመሸፈን የሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነትን ማብሰር የሚያስችሉ ተጨባጭ ተግባራትን እያከናወነች መሆኑን የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም(ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ኢትዮጵያ እልፍ ጸጋዎች፣ እምቅ አቅሞች፣ ብሩህ ተስፋዎች፣ ተዝቀው የማያልቁ እሴቶችና ባለታሪክ ህዝቦች ያሏት ሀገር ናት፡፡

ይሁን እንጂ እነዚህ አቅሞቿና አንጡራ ሀብቶቿ ዜጎቿን ከድህነት ኢትዮጵያን ከተረጂ ሀገራት መደብ ሳያወጧት ዓመታት ነጉደዋል፡፡

ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት በስንዴ ልማት፣ በሌማት ትሩፋት፣ በአረንጓዴ አሻራና በሌሎችም ሀገራዊ ጉዳዮች የተጀመሩ ኢኒሼቲቮች ተስፋ ሰጭ ውጤቶችን እያመጡ ነው፡፡

የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀሳብ አመንጪነት የሰብዓዊ ድጋፍ በራስ አቅም እሳቤ  እየተተገበረ ነው፡፡

ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ምንም ያልጎደላት ምንም ያላነሳት ሆና እያለ ለምን ተረጂ፣ ለማኝ ትሆናለች ከሚል ዕሳቤ የመነጨ ኢኒሼቲቭ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢኒሼቲቩ ተረጅነትና ጠባቂነት ወዴት እየወሰደን ነው ከሚል ቁጭት በመነሳት መጀመሩን ገልጸው፤  ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ከመቻል ባለፈ የክብር የነጻነትና የሀገር ሉዓላዊነት ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ መንግሥት ተረጂነትን ለማስቀረትና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በግብርናው መስክ ተጨባጭ ለውጦችን ማስመዝገቡን ገልጸዋል፡፡

በዚህም ኢትዮጵያ ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም በመሸፈን የሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነትን ማብሰር የሚያስችል የሚጨበጥ ተግባር እያከናወነች መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአደጋ ምላሽ ፈንድ በማቋቋም፣ የሎጂስቲክ ስርዓቱን በማሳለጥና ከውጭ የሚገባውን ስንዴ በማስቀረት ክልሎች የመጠባበቂያ ክምችታቸውን እያሳደጉ ነው ብለዋል፡፡

ከዚህም ባለፈ ለረጅም ዘመን እሴት ሆኖ የቀጠለውን የቤተሰብ ኃላፊነትና የማህበረሰብ አጋርነት ተቋማዊ ይዘት እንዲኖረው እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ 10 ክልሎች ሰብዓዊ ድጋፍን በራሳቸው አቅም መሸፈን መቻላቸውን የገለጹት ኮሚሽነሩ፥ አሁን ላይ ከውጭ የምናስገባው ስንዴ የለም ብለዋል።

ኢትዮጵያ ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን የጀመረችው ጉዞ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አመራር ሰጪነት በከፍተኛ ተነሳሽነት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸው፤ በስኬታማ ምዕራፍ ላይ  እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም