ወጣቶችን በልማት ተጠቃሚ የሚያደርግ የፖሊሲ አማራጭ ያለውን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቶችን በልማት ተጠቃሚ የሚያደርግ የፖሊሲ አማራጭ ያለውን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል
ሰመራ፤ ሚያዚያ 5/2018 (ኢዜአ)፦ ወጣቶችን በልማት ተጠቃሚ የሚያደርግ የፖሊሲ አማራጭ ያለውን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል ሲሉ የሰመራ ሎጊያ ከተማ ወጣቶች ተናገሩ።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ከየካቲት 28 ቀን 2018 ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው የመራጮች ምዝገባ እስከ ሚያዝያ 14 ቀን 2018 ዓ.ም መራዘሙ ይታወሳል።
በዚሁ መሰረት በአፋር ክልል የሰመራ ሎጊያ ከተማ ወጣቶችም በምርጫው በንቃት በመሳተፍ ሀገራዊ ልማትን ለማስቀጠል እና የወጣቶችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ የፖለቲካ አማራጭ ያለውን ፓርቲ ለመምረጥ ካርዳቸውን እየወሰዱ መሆኑን ነው የተናገሩት።
ለመምረጥ የሚያስችላቸውን የምርጫ ካርድ የወሰዱ የከተማ አስተዳደሩ ወጣቶች ለኢዜአ እንደተናገሩት የምርጫ ካርድ መውሰድ አማራጭ ሀሳብ ያለውን ፓርቲ ለመምረጥ መሰረታዊ ጉዳይ ነው።
ወጣት ሃጂ አብዱልለጢፍ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያላቸውን የፖሊሲ አማራጮች በሚዲያ በሚያደርጉት ክርክሮች በንቃት እየተከታተልኩ ነው ብሏል።
ይህም በተለይም የወጣቶችን ጉዳይ ትኩረት አድርጎ የሚንቀሳቀሰውን ፓርቲ ለመምረጥ እንደሚያስችለው ጠቅሶ በምርጫው በንቃት ለመሳተፍም ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሯል ብሏል።
ሌላኛው የከተማው ወጣት አብዱ መሐመድ በምርጫው ለመሳተፍ የሚያስችለውን ካርድ መውሰዱን ተናግሯል።
በካርዱም ይበጀኛል የሚለውንና የወጣቶችን ሁለንተናዊ ጥያቄዎች ለመመለስ የሚሰራን ፓርቲ ለመምረጥ ከወዲሁ መዘጋጀቱን ጠቁሟል ።
የመራጮች ካርድ መውሰዱ ለዴሞክራሲያዊ ግንባታ የበኩሉን ለማበርከትና የዜግነት ግዴታውን ለመወጣት መሰረት በመሆኑ ይህንኑ ተግባራዊ ማድረጉንም አክሏል።
የመራጭነት ካርድ መውሰዴ ይጠቅመኛል የምለውን ፓርቲ እንድመርጥ ያስችለኛል ያለው ደግሞ ወጣት የሱፍ መሐመድ ነው።
በዚህም በምርጫው በንቃት በመሳተፍ ሀገራችን የጀመረችውን የልማት ጉዞ ከግብ ለማድረስና የወጣቶችን ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥ አማራጭ ፖሊሲ ያለውን ፓርቲን ለመምረጥ ተዘጋጅቻለሁ ሲል ተናግሯል።