የሐረር ከተማ ነዋሪዎች በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጭነት ካርድ በመውሰድ ድምጻቸውን ለመስጠት ከወዲሁ ተዘጋጅተዋል - ኢዜአ አማርኛ
የሐረር ከተማ ነዋሪዎች በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጭነት ካርድ በመውሰድ ድምጻቸውን ለመስጠት ከወዲሁ ተዘጋጅተዋል
ሐረር ፤ ሚያዚያ 5/2018 (ኢዜአ)፦በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ መሳተፍ የሚያስችላቸውን የመራጭነት ካርድ በመውሰድ ድምጻቸውን ለመስጠት ከወዲሁ መዘጋጀታቸውን የሐረር ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ከየካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በየምርጫ ጣቢያዎች የመራጮች ምዝገባ እየተካሄደ ነው።
በዚህም በሐረሪ ክልል የሚገኙ ነዋሪዎች በምርጫው ለመሳተፍ የሚያስችላቸውን የመራጭነት ካርድ በመውሰድ ላይ ናቸው።
ከከተማው ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ፍሬህይወት አባይነህ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ከዚህ ቀደም በነበሩት አራት ሀገራዊ ምርጫዎች ላይ በመሳተፍ ይሆነኛል፣ ይበጃል የሚሉትን ፓርቲ መምረጣቸውን አስታውሰዋል።
በመጪው ግንቦት በሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ለመሳተፍ ከወዲሁ መዘጋጀታቸውን ጠቁመው፤ ለዚህም የመራጭነት ካርድ መውሰዳቸውን እና ድምጻቸውንም ለሀገር ልማትና እድገት ይሰራል ብለው ለሚያምኑት ፓርቲ እንደሚሰጡ ተናግረዋል።
የከተማው ነዋሪ አቶ ሀብታሙ ሲፋ በበኩላቸው፤ የዜግነትና ህገ መንግስታዊ መብታቸውን በመጠቀም በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለመሳተፍ የመራጭነት ካርድ እንደወሰዱ ተናግረዋል።
በሚዲያ አማራጮች የሚተላለፈውን የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክር በአግባቡ በመከታተል ላይ እንደሚገኙ የተናገሩት አቶ ሀብታሙ፤ ይሆነኛል ለሚሉት ፓርቲ ድምጻቸውን ለመስጠት መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።
ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንደሚገባም ተናግረዋል።
በምርጫው የነቃ ተሳትፎ ለማድረግ የምንፈልገውን ፓርቲ ለመምረጥ የሚያስችል ካርድ ወስደናል ያሉት ደግሞ አጀባ አደም ናቸው።
የሚበጀንን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል ያሉት አጀባ፤ ምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊ እንዲሆን የበኩላቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል።