በኢዜአ ዐይን …! - ኢዜአ አማርኛ
በኢዜአ ዐይን …!
በምግብ ራስን የመቻል ጉዞ አንዱ ምሰሶ - የስንዴ ልማት
በሙሴ መለሰ
ስንዴ በኢትዮጵያ በከፍትኛ ደረጀ ከሚመረቱና ለግብይት ከሚውሉ የሰብል ምርቶች መካከል በቀዳሚነት ይጠቀሳል። በዚህም መሠረት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከፍተኛ የስንዴ አምራች ከሆኑ ሀገራት መካከል በግንባር ቀደምነት ትጠቀሳለች።
ከ2011/2012 የምርት ዘመን በፊት ኢትዮጵያ በመኸር የምታለማው ስንዴ ከ1 ነጥብ 7 ሚሊየን ሔክታር ያልበለጠ ነበር። የበጋ መስኖ ስንዴ ሲጀመርም 3 ሺህ ሔክታር ብቻ እንደነበር መረጃዎች ያመላክታሉ።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በመኸር፣ በበጋ መስኖ እና በበልግ ወቅት 7 ነጥብ 4 ሚሊየን ሔክታር መሬት ላይ ስንዴ እያለማች እንደምትገኝ የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያስረዳል።
ሚኒስቴሩ የ2018 ዓ.ም የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትን አስመልክቶ ባወጣው መረጃ፤ 4 ነጥብ 29 ሚሊየን ሔክታር መሬት ላይ ስንዴ በማልማት ከበጋ መስኖ ስንዴ 175 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱን መግለጹ ይታወሳል።
በኢትዮጵያ በአብዛኛው የስንዴ ምርት የሚመረተው በአነስተኛ አርሶ አደሮች ነው። ባለፉት ዓመታት ግን የሜካናይዝድ እርሻ የስንዴ ምርቱን በእጥፍ እንደጨመረው ይገለጻል።
መንግሥት መስኖን በመጠቀም ስንዴን በዓመት አንድ ጊዜ ከማምረት ወደ ሦስት ጊዜ ማምረት የሚቻልበትን አሰራር በመፍጠር የሀገሪቱን ምርታማነት ለማሳደግ እየሠራ ይገኛል።
ኢትዮጵያ ዓመታዊ የስንዴ ፍላጎቷ ከ107 ሚሊየን ኩንታል በላይ ነው። ይህንን ፍላጎቷን ለመሙላት ለዓመታት ከ700 ሚሊየን ዶላር እስከ 1 ቢሊየን ዶላር ለስንዴ ግዥ ወጪ ታደርግ ነበር።
ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ከዓመታዊ የስንዴ ፍላጎቷ ከ25 እስከ 30 በመቶ የሚሆነውን ትሸፍን የነበረውም ከውጭ በምትገዛው ስንዴ ነበር።
መንግሥት የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትን በማስፋፋትና በየዓመቱ የሚመረትበትን ዙር በመጨመር ኢትዮጵያ የስንዴ ፍጆታዋን ሙሉ በሙሉ እንድትሸፍን በትኩረት ሲሠራ ቆይቷል።
በዚሁ በ2014 ዓ.ም ኢትዮጵያ ከውጭ ሀገር ስንዴ ማስገባት አቆመች።
ኢትዮጵያ በስንዴ ልማት ያገኘችው ውጤት ከውጭ ማስገባትን ማስቆም ብቻ አልነበረም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ራስን ብቻ ሳይሆን ኤክስፖርት የማድረግ ዐቅም እንዳላት በመግለጽ፤ ስንዴ ወደ ውጪ መላክ እንደሚገባ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስቀመጡት ሀገራዊ ግብ መሰረት ኢትዮጵያ የካቲት 5 ቀን 2015 ዓ.ም ወደ ውጭ የመላክ ተግባርን በይፋ አስጀምራለች።
የስንዴ ኤክስፖርቱ ኢትዮጵያ ገጽታዋን የሚለውጥ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ መግባቷን የሚያመላክት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ ገልጸው ነበር።
ኢትዮጵያ በ2015 ዓ.ም የሀገር ውስጥ ፍጆታዋን ሸፍና 32 ሚሊየን ኩንታል ስንዴ ለውጭ ገበያ የማቅረብ ዐቅም እንዳላት ብሔራዊ የማክሮ ኢኮኖሚና የኤክስፖርት ኮሚቴ አረጋግጧል።
ኮሚቴው የሀገራዊ የነፍስ ወከፍ ፍጆታና የሀገሪቱን አጠቃላይ የምርት ሚዛን በማጥናት ከፍጆታ የሚተርፍ 32 ሚሊየን ኩንታል ስንዴ ወደ ውጭ መላክ እንደሚቻልም ተገልጿል።
38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ባሳለፍነው የካቲት ወር በሕብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ መካሄዱ የሚታወስ ነው።
በወቅቱም የአፍሪካ ሕብረት የግብርና፣ የገጠር ልማት፣ ብሉ ኢኮኖሚ እና የዘላቂ አካባቢ ኮሚሽነር ሞሰስ ቪላካቲ ከጉባዔው ጎን ለጎን በሰጡት መግለጫ፤ ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ያስመዘገበችው ስኬት ለአፍሪካ ተምሳሌታዊ የሆነ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ የስንዴ ምርታማነቷን በማሳደግ የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ከመሸፈን ባለፈ ለውጭ ገበያ ማቅረብ መቻሏን ሕብረቱ መመልከት መቻሉንም ተናግረዋል።
የአፍሪካ ሀገራት በዓመት ውስጥ ለምግብ ምርቶች ከሚያወጡት የውጭ ምንዛሬ ስንዴ ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዝም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ከውጭ የሚገባውን ምርት በሀገር ውስጥ ስንዴ መተካት እንደሚቻል በተግባር ያሳየችበት መንገድ የሚደነቅ ነው ብለዋል።
ኮሚሽነሩ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የኢትዮጵያን ተሞክሮ ወስደው ወደ ተግባር እንዲገቡ ጥሪ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ በስንዴ ልማት ሥራ ላይ እያሳየች ያለውን ሥራ አስፍታ ከቀጠለች በምግብ ራሷን የመቻል ሕልሟን የማሳካት እድሏ ሰፊ መሆኑንም ማመላከታቸው ይታወሳል።