የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 27ኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 27ኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 5/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 27ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ አራት ጨዋታዎች ይደርጋሉ።
ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ አዲስ አዳጊዎች ሸገር ከተማ እና ነገሌ አርሲ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ሸገር ከተማ በሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው 26 ጨዋታዎች በስድስቱ አሸንፎ በሰባቱ ተሸንፎ 13 ጊዜ አቻ ወጥቷል።
23 ግቦችን በጨዋታዎቹ ላይ ሲያሳርፍ 24 ጎሎችን አስተናግዷል። ቡድኑ በ31 ነጥብ 14ኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው ነገሌ አርሲ 26 ጨዋታዎችን አከናውኖ 11 ጊዜ ሲያሸንፍ በስድስቱ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ ዘጠኝ ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። 25 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 18 ጎሎች ተቆጥረውበታል።
ነገሌ አርሲ በ42 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ባለፉት ሁለት የሊግ ጨዋታዎች ያላሸነፈው ሸገር ከተማ ከወራጅ ቀጠና አካባቢ በመጠኑ እንዲርቅ ያደርገዋል።
በ26ኛ ሳምንት ከኢትዮጵያ መድን ጋር አንድ አቻ የተለያየው ነገሌ አርሲ ካሸነፈ ከሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሶስት ዝቅ ያደርጋል።
በሌላኛው መርሐ ግብር ሃዋሳ ከተማ ከከምድረ ገነት ሽሬ ምሽት 12 ሰዓት ላይ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ሃዋሳ ከተማ በውድድር ዓመቱ 26 ጨዋታዎችን አድርጎ በ11ዱ ሲያሸንፍ በሰባቱ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ ስምንት ጨዋታዎች አቻ ወጥቷል።
30 ግቦችን በ26ቱ ጨዋታዎች ላይ ሲያስቆጥር 21 ጎሎችን አስተናግዷል። ሃዋሳ ከተማ በ41 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል።
በሊጉ ካከናወናቸው 26 ጨዋታዎች መካከል ስድስቱን ያሸነፈው ምድረ ገነት ሽሬ በበኩሉ 10 ጊዜ ተሸንፏል። 10 ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል። 17 ግቦችን ሲያገባ 21 ጎሎች ተቆጥረውበታል።
ምድረ ገነት ሽሬ በ28 ነጥብ 18ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
ባለፉት ሶስት የሊጉ ጨዋታዎች ከድል የራቀው ሃዋሳ ከተማ ማሸነፍ በዋንጫ ፉክክሩ ለመቆየት የሚያስችለውን ወሳኝ ሶስት ነጥብ ያገኛል።
ካለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች አንዱንም ማሸነፍ ያልቻለው ምድረ ገነት ሽሬ ሶስት ነጥብ ማግኘት ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት በሚያደርገው ጥረት ወሳኝ የሚባል ነው።
አርባምንጭ ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ከቀኑ 10 ሰዓት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።
አርባምንጭ ከተማ በ22 ነጥብ የመጨረሻውን 20ኛ ደረጃን ይዟል። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ31 ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በ26ኛ ሳምንት በሀዲያ ሆሳዕና የ1 ለ 0 ሽንፈት ያስተናገደው አርባምንጭ ከተማ ማሸነፍ ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት በሚያደርገው ፉክክር ወሳኝ ሶስት ነጥብ ያስገኝለታል።
የ16 ጊዜ የሊጉ አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስ ካሸነፈ ሶስተኛ ተከታታይ ድሉን ያስመዘግባል።
ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ መቀሌ 70 እንደርታ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
መቀሌ 70 እንደርታ በ23 ነጥብ 19ኛ፣ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በ29 ነጥብ 17ኛ ደረጃን በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ።
ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች ከድል የራቀው መቀሌ 70 እንደርታ ማሸነፍ ላለመውረድ በሚያደርገው ትግል ወሳኝ ሶስት ነጥብ ያስገኝለታል።
በአንጻሩ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ያላሸነፈው ወልዋሎ ወደ ድል መንገድ ለመመለስ እና ሶስት ነጥብ ለማግኘት ይጫወታል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 27ኛ ሳምንት እስከ ሚያዚያ 7 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።
ሲዳማ ቡና በ48 ነጥብ ሊጉን እየመራ ነው።
አቤል ያለው ከሲዳማ ቡና በ11 ግቦች የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን እየመራ ይገኛል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ አዲስ ግደይ በ10 ጎሎች ይከተላል።