ማንችስተር ዩናይትድ ከሊድስ ዩናይትድ ጋር ጨዋታውን ያደርጋል - ኢዜአ አማርኛ
ማንችስተር ዩናይትድ ከሊድስ ዩናይትድ ጋር ጨዋታውን ያደርጋል
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 5/2018 (ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ32ኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሐ-ግብር በማንችስተር ዩናይትድ እና ሊድስ ዩናይትድ መካከል ዛሬ ይካሄዳል።
ጨዋታው ምሽት አራት ሰዓት ላይ በኦልድትራፎርድ ስታዲየም ይከናወናል።
ማንችስተር ዩናይትድ በ55 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ሊድስ ዩናይትድ በ33 ነጥብ 15ተኛ ደረጃን ይዟል።
ሁለቱ ክለቦች በፕሪሚየር ሊጉ ሲገናኙ የአሁኑ ለ32ኛ ጊዜ ነው።
ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው 31 ጨዋታዎች ማንችስተር ዩናይትድ 17 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል። ሊድስ በአራቱ ድል ሲቀናው በቀሪ 10 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።
በ31ዱ ጨዋታዎች ማንችስተር ዩናይትድ 64 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ ሊድስ ዩናይትድ 31ጎሎችን አስቆጥሯል።
ባለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች በነበራቸው የእርስበርስ ግንኙነት ማንችስተር ዩናይትድ ሶስት ጨዋታዎችን ሲያሸንፍ በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርተዋል።
ሊድስ ዩናይትድ ለመጨረሻ ጊዜ ማንችስተር ዩናይትድ በሊጉ ያሸነፈው እ.አ.አ በ2002 ነው።
ክለቡ ከ24 ዓመት በኋላ ዩናይትድን ለማሸነፍ ይጫወታል።
ሁለቱ ቡድኖች በዘንድሮው የውድድር ዓመት በ20ኛ ሳምንት ባደረጉት ጨዋታ አንድ አቻ መለያየታቸው የሚታወስ ነው።
በጊዜያዊ አሰልጣኝ ማይክል ካሪክ ጥሩ ጊዜ እያሳለፈ የሚገኘው ማንችስተር ዩናይትድ ካሸነፈ የሶስተኝነት ደረጃን በማጠናከር ሻምፒዮንስ ሊግ የመግባት እድሉን ያሰፋል።
ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች ያላሸነፈው ሊድስ ዩናይትድ ሶስት ነጥብ ከወራጅ ቀጠና ስፍራ በመጠኑም ቢሆን እንዲርቅ ያደርገዋል።