አትሌት ምስጋና ዋቁማ በዓለም አትሌቲክስ የርምጃ ሻምፒና ታሪክ ለኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ሜዳሊያ አስገኘ - ኢዜአ አማርኛ
አትሌት ምስጋና ዋቁማ በዓለም አትሌቲክስ የርምጃ ሻምፒና ታሪክ ለኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ሜዳሊያ አስገኘ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 4/2018 (ኢዜአ)፦ 31ኛው የዓለም አትሌቲክስ የርምጃ ሻምፒዮና በብራዚል ብራዚሊያ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የተሳተፉባቸው የፍጻሜ ውድድሮች ተደርገዋል።
በወንዶች የግማሽ ማራቶን የርምጃ ፍጻሜ ውድድር አትሌት ምስጋና ዋቁማ 1 ሰዓት ከ27 ደቂቃ ከ33 ሴኮንድ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ የብር ሜዳሊያ አግኝቷል።
አትሌት ምስጋና በኢትዮጵያ ስድስተኛ የሻምፒዮናው ተሳትፎ የመጀመሪያውን ሜዳሊያ አስገኝቷል።
ጣልያናዊው ፍራንቼስኮ ፎርቹናቶ አንደኛ ወጥቷል። ብራዚላዊው አትሌት ካዮ ቦንፊም ሶስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።
ከ20 ዓመት በታች የ10 ኪሎ ሜትር ሴቶች የፍጻሜ ውድድር ህይወት አምባው በ48 ደቂቃ ከ52 ሴኮንድ ዘጠነኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። በርቀቱ የግል ምርጥ ሰዓቷን አስመዝግባለች።
ቻይናዊቷ አትሌት ዩቶንግ ያንግ አንደኛ ወጥታለች።
እንዲሁም ጣልያናዊቷ ሴሬና ዲ ፋቢዮ ሁለተኛ፣ ቻይናዊቷ ሊሁዋ ኒ ሶስተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።
በ10 ኪሎ ሜትር ከ20 ዓመት በታች ወንዶች ፍጻሜ አብዱሰላም አብዱልወሀብ 42 ደቂቃ ከ21 ሴኮንድ 11ኛ ደረጃን ይዞ ጨርሷል። በርቀቱ የግል ምርጥ ሰዓቱን አስመዝግቧል።
ቻይናዊው አትሌት ሁዋጂያ ፑ አንደኛ በመውጣት የወርቅ ሜዳሊያ አግኝቷል።
አውስትራሊያዊው ኢሳቅ ቢክሮፍት ሁለተኛ፣ ጣልያናዊው አሌሲዮ ኮፖላ ሶስተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።
ኢትዮጵያ በተሳተፈችባቸው ሶስት የፍጻሜ ውድድሮች አንድ የብር ሜዳሊያ በማግኘት አጠናቃለች።
በሻምፒዮናው ተሳትፎ ታሪኳ የመጀመሪያ ሜዳሊያ አግኝታለች።