ቀጥታ፡

ፋሲካ -አብሮነት የሚደምቅበት የደስታ በዓል

በኢትዮጵያ የፋሲካ በዓል በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በታላቅ ድምቀት የሚከበር በዓል ነው። የትንሳኤ በዓል የሚከበረው ከ55 ቀናት የጾም ወቅት በኋላ ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች እነዚህን ቀናት ፈጣሪያቸውን በጾምና ጸሎት ከመለመን ባለፈ ከሥጋ፣ ከወተትና መሰል የእንስሳት ተዋጽኦ ምግቦች ታቅበው ነው የሚያሳልፉት።

የትንሣኤ በዓል ከመድረሱ በፊት ያለው አንድ  ሳምንት "ሰሞነ ሕማማት" በመባል ይታወቃል። የእምነቱ ተከታዮች በሰሞነ ሕማማት ኢየሱስ ክርስቶስ ያሳለፈውን መከራና ስቃይ በማሰብ በቤተ ክርስቲያን በስግደት፣ በጸሎትና በጾም በተለየ ሁኔታ ያሳልፋሉ። ምእመናን በእለተ አርብ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች መዳን ብሎ በቀራኒዮ አደባባይ የከፈለውን መከራ፣ ግርፋትና ስቅላት በማሰብ በስግደት፣ በጸሎትና በተለያዩ ሃይማኖታዊ ስርዓቶች ያሳልፋሉ።

የትንሳኤ (የፋሲካ) በዓልም ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትል ድል አድርጎ መነሳቱን ተከትሎ የሚከበር ነው። ትንሳኤው ይቅርታ፣ ለሰው ለጆች መዳን የተከፈለ ፍቅርና መስዋዕትነት ጎልቶ የሚታይበት ነው። በመሆኑም ፋሲካ ሞትን ድል በመንሳት በትንሳኤ የምስራች የተበሰረበት ታላቅ በዓል ነው ማለት ይቻላል። ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን በትንሳኤ የለወጠበት ለሰው ልጅም ፍቅርን በቤዛነት ተክቶ ያሳየበት ዕለት ነው። 

ዕለቱ ትንሳኤ ብርሀን የታየበት በመሆኑ በትንሣኤ ዋዜማ ቅዳሜ ምሽት ምዕመናን ነጭ ልብስ ለብሰው ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ ሌሊቱን በጸሎትና በተለያዩ ሃይማኖታዊ ስርአቶች ያሳልፋሉ። 

የሌሊቱ ቅዳሴና ስርአተ ፀሎት ከተጠናቀቀ በኋላ ምዕመናን ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ጾም ይፈታሉ። ከቅባት ምግቦች ለሁለት ወራት በመቆጠብ ያሳለፉበት ወቅት በመሆኑም በትንሳኤ ሌሊት ዶሮ በመብላት ጾማቸውን ይፈስካሉ። በበዓሉ ቀንም በነጭ የሀበሻ ልብስ ደምቀው ይታያሉ።

በዓሉ ከሃይማኖታዊ ሥርአቱ ባለፈ የአብሮነት፣ የፍቅርንና የመተሳሰብ እሴት ያለው ነው። ዘመድ አዝማድ በመጠራራትና ከጎረቤት ጋር አብሮ በመብላትና በመጠጣት የሚያሳልፉት ነው። ቤት ያፈራውን በመቋደስ በዓሉን በአብሮነት በደስታ ያሳልፋሉ።  

የፋሲካ በዓል ማህበራዊ ትስስር የሚገለጥበትና አብሮነት የሚደምቅበት የደስታ በዓል ነው። በተለይ በፋሲካ በዓል ለዶሮ ወጥ ልዩ ትኩረት ይሰጣል። ፋሲካና ዶሮ ወጥ ጥብቅ የሆነ ባህላዊ ቁርኝት ያላቸው በመሆኑ አንዱ የበዓሉ ማድመቂያ ተደርጎ ይወሰዳል። ከዚህ በተጨማሪ የበሬ ቅርጫ፣ በግ፣ ፍየል፣  ዳቦና ጠላ እንደየ አቅም በማዘጋጀት ይከበራል። በአንዳንዶች ዘንድም ከገብስ ብቻ የሚዘጋጅ "ኬኔቶ" የተሰኘ (ከአልኮል ነፃ የሆነ መጠጥ) በማዘጋጀት በአማራጭነት ይቀርባል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም