ቀጥታ፡

ሀገርን የማልማት ሥራ በበዓልና በእረፍት ቀናት ሳይገታ ተጠናክሮ ይቀጥላል 

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 4/2018 (ኢዜአ)፦ ሀገርን የማልማት ሥራ በበዓልና በእረፍት ቀናት ሳይገታ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ እየተገነባ በሚገኘው የኢንዱስትሪ ክላስተር የሥራ ቦታ በመገኘት በግንባታው ላይ ለሚሳተፉ ሠራተኞች ማዕድ አጋርተዋል።


 

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ጊዜ፤ በተለወጠ የሥራ ባሕል በርካታ መሠረተ ልማቶች በጥራት እየተገነቡ መሆኑን ተናግረዋል።

እየሰራን ሀገርን እየገነባን በዓልን እናከብራለን ያሉት ከንቲባዋ መስራት የሚያስከብር ተግባር መሆኑንና ከድህነት ለመውጣት በበዓል፣ በእረፍትም ሆነ በሌሊት ጠንክሮ መስራት የግድ እንደሚል አስገንዝበዋል።

ይህ የኢንዱስትሪ ክላስተር ፕሮጀክት በአሁኑ ወቅት ለ13 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን ገልጸዋል። 

ግንባታውን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ ሠራተኞች የበዓል ቀናትን ጨምሮ በከፍተኛ ተነሳሽነት እየሰሩ መሆኑንም አክለዋል።


 

በዓል ምሉዕ የሚሆነው ከለውጥና ከብልፅግና ጋር ሲያያዝ ነው ያሉት ከንቲባዋ፤ የማዕከሉ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ በአሁኑ ወቅት በመጠናቀቅ ላይ እንዳለ ገልጸዋል።

ግንባታው ተጠናቆ ማዕከሉ ሥራ ሲጀምር ለበርካታ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል ከመፍጠሩም በላይ ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ለውጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።

ሠራተኞቹ በበዓላትም ሆነ በእረፍት ቀናት ሳይወሰኑ ሀገርን ለማልማት እያሳዩ ላለው ትጋት ምስጋና አቅርበዋል።

በግንባታው ላይ እየተሳተፉ ያሉት ሠራተኞች በሰጡት አስተያየት የተደረገላቸው የማዕድ ማጋራት የሥራ ተነሳሽነታቸውን እንደሚጨምረውና ለሀገር ግንባታ ያላቸውን ቁርጠኝነት እንደሚያጠናክረው ገልጸዋል።

እንዲህ ያሉ የቅርብ ክትትልና ድጋፎች ፕሮጀክቱ በተቀመጠለት የጊዜ ገደብና ጥራት እንዲጠናቀቅ ትልቅ አቅም እንደሚሆኑም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም