በዓላት ሲከበሩ የታመሙትን በመጠየቅ፣ የተቸገሩትን በመርዳትና አብሮነትን በማሳየት ሊሆን ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በዓላት ሲከበሩ የታመሙትን በመጠየቅ፣ የተቸገሩትን በመርዳትና አብሮነትን በማሳየት ሊሆን ይገባል
ባሕር ዳር፤ሚያዚያ 4/2018 (ኢዜአ)፦ በዓላት ሲከበሩ የታመሙትን በመጠየቅ፣ የተቸገሩትን በመርዳትና አብሮነትን በማሳየት ሊሆን ይገባል ሲሉ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ ተናገሩ።
የአማራ ክልል የተለያዩ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ባህር ዳር በፈለገ ሕይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በመገኘት ታማሚዎችን በመጠየቅ ለታካሚዎች እና አስታማሚዎች ማዕድ አጋሩ።
በዚሁ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ፤ ሆስፒታሉ የተሻሻለ እና ዘመናዊ የህክምና አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
የህክምና አገልግሎቱ እንዳለ ሆኖ በተለይም በዓላትን ስናከብር ታማሚዎችን አስታውሶ መጠየቅና አብሮነትን ማሳየት ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም በዓላት ሲከበሩ የታመሙትን በመጠየቅ፣ የተቸገሩትን በመርዳትና አብሮነትን በማሳየት ሊሆን ይገባል ብለዋል።
የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ በሆስፒታሉ በመገኘት የታመሙትን መጠየቃቸውንና ማእድ ማጋራታቸውን ተናግረዋል።
የፈለገ ሕይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሥራ አሥኪያጅ ዐቢይ ፍሰሐ በበኩላቸው፤ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች የፋሲካ በዓልን ምክንያት በማድረግ በሆስፒታሉ በመገኘት በመጠየቅና ማእድ በማጋራት አብሮነታቸውን በማሳየታቸው አመስግነዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊና የሆስፒታሉ ቦርድ ሰብሳቢ ፍሰሐ ደሳለኝ፤ የበዓላት አከባበር በተለይም ማህበራዊ እሴቱ አብሮነት፣ መረዳዳትና መተጋገዝን መሰረት ያደረገ መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም የትንሳኤ በዓልን ስናከብር የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳትና የታመሙትን በመጠየቅ መሆን ይኖርበታል ብለዋል።