ቀጥታ፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ የትንሣኤን በዓል ምክንያት በማድረግ 27ኛውን የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል ሥራ አስጀመሩ   

አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 4/2018 (ኢዜአ)፦የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የትንሣኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ 27ኛውን የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል በጉለሌ ክፍለ ከተማ በይፋ መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት፤ በአዲስ አበባ የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ያስቻሉ ግዙፍ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች መገንባታቸውን ገልጸዋል።


 

ሰው ተኮር ፕሮጀክቶችንም በጥራትና በፍጥነት በመገንባት በማህበራዊ ችግር ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ለአብነትም የመዲናዋ የምገባ ማዕከላት እጅ አጠር ዜጎች ማህበራዊ ድጋፍ የሚያገኙበትን ወሳኝ ዕድል በመፍጠር ከፍተኛ ጠቀሜታ እያበረከቱ እንደሚገኝ አንስተዋል።


 

27ኛው የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል በጉለሌ ሶስተኛው ቅርንጫፍ መሆኑን ገልጸው፤ማዕከሉ በርካታ አቅመ ደካማ ወገኖች በቀን አንድ ጊዜ የምግብ አገልግሎት የሚያገኙበትን ዕድል እንደሚፈጥር ጠቅሰዋል።

በአዲስ አበባ የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል ግንባታ ስኬት ከፍተኛ ድጋፍ እያደረጉ ለሚገኙ ባለሃብቶችና በጎ አድራጊዎችም ምስጋና አቅርበዋል።

በቀጣይም የዜጎች የመረዳዳትና መደጋገፍ እሴት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።


 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምገባ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ፀዳለች ሚካኤል በበኩላቸው ፤ በምገባ ማዕከላት የሚከናወነው የምገባ መርሐ ግብር በበዓላት ወቅት ብቻ ሳይሆን በቋሚነት የሚከናወን በመሆኑ ለብዙዎች የሕይወት ተስፋ እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል።


 

አስተያየታቸውን የሰጡ የማዕከሉ ተጠቃሚዎች በበኩላቸው፤ ከከንቲባዋ ጋር በዓልን በማሳለፋቸው መደሰታቸውን ገልፀው ማዕከሉ አረጋውያንና ሕፃናት የእለት ጉርሳቸውን አጥተው እንዳይቸገሩ ትልቅ እፎይታ የሚፈጥርላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም