ቀጥታ፡

በኅብረትና ጽናት የሚቀረጽ ብርሃን፤ የኢትዮጵያ ትንሣኤ

በኅብረትና ጽናት የሚቀረጽ ብርሃን፤ የኢትዮጵያ ትንሣኤ

በቀበኔሳ ገቢሳ

ትንሣኤ ለሰው ልጅ ተስፋን፣ ዘለዓለማዊ ሕይወትን እና ከኃጢአት ነፃ መውጣትን የሚያበስር ኃይማኖታዊ በዓል ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ በመነሳቱ የሰው ልጅ የዘለዓለም የሕይወት አክሊልን ተስፋ ያደረገበት፣ የእግዚአብሔር ፍቅር የተገለጠበት እንዲሁም የሰው ልጅ ከዘለዓለም ሞትና ከኃጢአት ባርነት ነፃ የወጣበት የድኅነት፣ የፍቅር፣ የጽናትና የተስፋ ብርሃን ብስራት ነው፡፡

የትንሣኤ በዓል ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ የመነሳቱ ታላቅ ምሥጢር የሚታሰብበት ብቻ አይደለም፤ ይልቁንስ የሰው ልጅ ከውርደት ወደ ክብር፣ ከኃጢያት ባርነት ወደ ድኅነት እንዲሁም ከጉስቁልና ወደ ብሩህ ተስፋ የተሸጋገረበት የድል አዋጅ ነው። በዕለቱም በሞት ላይ ሕይወት፣ በሐዘን ላይ ደስታ፣ በቂም ላይ ይቅርታ ተበስሮበታል። ከበዓላት ሁሉ የላቀ የነጻነት ተምሳሌት ነው ትንሣኤ።

👉የትንሣኤ ሕያው አስተምሮ በዕለት ተዕለት ሕይወት

ትንሣኤ ሲከበር ከሥርዓተ አምልኮ ባለፈ፣ በዓሉ የሚሰጠውን ታላቅ አስተምሮ ማጤን ይገባል። ትንሣኤ በየቀኑ ካለንበት ድካምና ውድቀት በአዲስ መንፈስ የመነሳት አቅም ነው። በዓሉ የሚያስተምረንን የጽናት፣ የተስፋና የአብሮነት ዕሴት በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ መኖር ያስፈልጋል። ለዚህም የተቸገሩን መርዳት፣ የታመሙትን መጠየቅና የተጣሉትን ማስታረቅ የበዓሉን ትርጉም እውነተኛ ያደርገዋል።

👉የኢትዮጵያ ትንሣኤ፤ በፈተና የጸና ብርሃን

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዓሉን በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት፤ "የዘንድሮውን የትንሣኤ በዓል የምናከብረው ሀገራችን ኢትዮጵያ በፈታኝ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ ሆና እያለች ነው። መንገዳችን ረጅም፣ ጉዟችንም እሾህ የበዛበት ሊሆን ይችላል። ብርሃን እንዳናይ የሚጋርዱ፣ በጨለማ ወጥመድ ሊያሥሩን የሚሞክሩ መሰናክሎች ቢበዙም፣ እምነታችን ግን ከሕማማት በኋላ ትንሣኤ እንደሚመጣ ነው" ብለዋል፡፡

"ኢትዮጵያ ዛሬም ትንሳኤዋን እያየች ነው። መቃብሯ ተከፍቷል፤ ማኅተሙም ተሰብሯል። የትንሣኤውን ዜና ሊያደበዝዙ የሚሞክሩ የውሸት ወሬዎችና ተስፋ አስቆራጭ ትረካዎች የሀገራችንን የብርሃን ጉዞ ሊገቱት አይችሉም። ትንሳኤው እውነት ነው፤ ብርሃኑም የማይቀለበስ ሀቅ ሆኗል" ሲሉም አረጋግጠዋል፡፡

👉ዴሞክራሲ እና ብሔራዊ ምክክር፤ የተስፋ ምዕራፎች

የኢትዮጵያ ትንሣኤ አንዱ መገለጫ ዴሞክራሲን የመገንባት ጽናት ነው። ትንሣኤ ያለ ሕማማት እንደማይገኝ ሁሉ ዴሞክራሲ ያለ ፈተና በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ዴሞክራሲ የሚገነባው በጽናት እንጂ በፍርሃት አይደለም። ዴሞክራሲን እየገነባን በትዕግሥትና በቆራጥነት ወደ ተስፋዋ ምድር እንደርሳለን።

አሁን ያለው የዓለም ነባራዊ ሁኔታ ጦርነት፣ የኢኮኖሚ ቀውስና ማህበራዊ አለመረጋጋት የትንሳኤን ትምህርት ከመቼውም ጊዜ በላይ አስፈላጊ ያደርገዋል፡፡ ችግሮችን በብቸኝነት የምንወጣበት ጊዜ አብቅቷል። ዛሬ እንደህዝብ የሚያስፈልገን ከ"እኔ" ወደ "እኛ" መሸጋገር፣ የግል ፍላጎትን ለጋራ ስኬት መስዋዕት ማድረግ ግድ የሚልበት ወቅት ላይ ነን። የአንድነት ጉዟችንን በማጠናከር ዓለም አቀፋዊና ሀገራዊ ጫናዎችን ለመቋቋም በጋራ መቆም ይገባናል። የተቸገሩትን በመርዳት፣ የታመሙትን በመጠየቅና የተጣሉትን በማስታረቅ  የተግባር አብሮነትን በማሳየት የበዓሉን እውነተኛ ትርጉም መግለጥ ይገባል፡፡

👉ምርጫ፤ ከኢትዮጵያን ትንሣኤ ማብሰሪያዎች አንዱ ምዕራፍ

ትንሣኤ ሞት ድል የተነሳበትና ተስፋ የታደሰበት ዕለት ነው። እኛም በምርጫ ካርዳችን የሃሳብ ልዩነትን በዴሞክራሲያዊ አንድነት ድል በማድረግ የኢትዮጵያን የብልፅግና ትንሳኤ እናረጋግጣለን። በትንሣኤ በዓል የምንማረው ይቅርታና ጽናትም ለምርጫችን ስኬት አቅም ይሆናል። በኅብረት የምንሰጠው ድምፅም የነገዋን ብሩህ ኢትዮጵያ የመቅረጽ ኃይል በእጃችን መሆኑን ያሳያል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመልዕክታቸው "ምርጫ የኢትዮጵያን ትንሣኤ ማብሰሪያዎች አንዱ ምዕራፍ ነው። ትንሣኤን ያለ ሕማማት እንደማናስበው ሁሉ ዴሞክራሲንም ከውጣ ውረድ ነጥሎ ማየት አይቻልም። በዓለም ላይ በደልዳላ መንገድ ተጉዞ ዴሞክራሲን የገነባ ሀገር የለም። ዴሞክራሲና ብልፅግና ያለ ጽናት አይሳኩም። ከእኛ በፊት ዐመጻውን በትዕግሥት የመከቱ ተሻግረዋል፤ ሑካታውን በጽናት ያለፉ አሳክተዋል። ብንመኝም ፈተናውን አናስቀርም፤ መጽናት ግን እንችላለን። ከድኅነት መውጫው ብርታታችን፣ ወደ ዴሞክራሲ መድረሻችው ትዕግሥታችን እንደሆነ አምነን ለኢትዮጵያ ትንሣኤ በሙሉ ልባችን እንትጋ!!" ብለዋል።

👉የወደፊት እጣ ፈንታችን በእጃችን

ከፊታችን የሚጠብቁን ሀገራዊ ምክክርና የ2018 ዓ.ም ጠቅላላ ምርጫ የኢትዮጵያን የወደፊት መጻኢ ዕድል የሚወስኑ ታላላቅ ሁነቶች ናቸው። እነዚህ ሂደቶች ስኬታማ የሚሆኑት እያንዳንዱ ዜጋ የድርሻውን ሲወጣ ብቻ ነው።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር በልባችን ውስጥ ይቅርታና አብሮነት ሲነግስ ብቻ ግቡን ይመታል። ትንሣኤ ሞት ድል የተነሳበት እንደሆነው ሁሉ፣ በምክክሩም ጥልን፣ ጥርጣሬን፣ ያለመግባባት መንፈስን ድል መንሳት ይገባል፤ ቅንነት፣ ተስፋና መተሳሰብ ለምክክሩ ስኬት የመተማመኛ ቁልፎች ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ 2018 ዓ.ም  ደግሞ የዜጎች ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ ማሳያ አንጓ ነው፤ የዜጎች ነፃ ተሳትፎ መብታቸውን የሚያስከብሩበት ፍላጎታቸውን የሚያረጋግጡበት ማረጋገጫ ማህተም ጭምር፡፡ ዜጎች የመምረጥና የመመረጥ መብታቸውን የሚያስከብሩበት፤ የሌላውን ሃሳብ አክብረው የራሳቸውን የሚያስከብሩበት ለኢትዮጵያ ትንሣኤ በጋራ የሚቆሙበት መድረክ ነው፡፡

ትንሣኤ የድልና የነጻነት በዓል ነው። ይህንን ታላቅ ዕለት ስናከብር ያለፈውን ቁስል ሽረን፣ ለነገ ተስፋ ሰንቀን መሆን አለበት። እርስ በእርስ በመደጋገፍ፣ ችግሮችን በንግግር በመፍታት ለሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ስኬታማነት የድርሻችንን መወጣት ይገባናል። የተሻለችና የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመገንባት በጋራ እንቁም!

መልካም የትንሳኤ በዓል!!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም