የገንዳ ውኃ ከተማ ወጣቶች በዓሉን አብሮነትን በሚያጠናክር መልኩ እያከበሩ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የገንዳ ውኃ ከተማ ወጣቶች በዓሉን አብሮነትን በሚያጠናክር መልኩ እያከበሩ ነው
ገንዳ ውኃ፤ሚያዚያ 4/2018 (ኢዜአ)፡- የትንሳኤ በዓልን አቅመ ደካማ ወገኖች በማሰብና አብሮነትን በሚያጠናክር መልኩ እያከበሩ መሆናቸውን የገንዳ ውኃ ከተማ ወጣቶች ገለጹ።
ወጣቶቹ የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ ለአቅመ ደካሞች፣ ለአረጋውያንና ለተቸገሩ የህብረተሰብ ክፍሎች የቅርጫ ሥጋ አከፋፍለዋል።
ከድጋፍ አድራጊ ወጣቶች መካከል ኤልያስ ጋሻው እንደገለጸው የማዕድ የማጋራቱ ተግባር ላለፉት ዓመታት ተጠናከሮ ቀጥሏል።
በዚህም ጧሪና ደጋፊ የሌላቸው አረጋውያን፣ አሳዳጊ የሌላቸው ሕፃናትና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድርጋቸውን ገልጸዋል።
በዛሬው እለትም ወጣቶች ከራሳቸው ባዋጡት እንዲሁም ከህብረተሰቡና ከተቋማት ባሰባሰቡት ገንዘብ የእርድ እንስሳት ገዝተው የቅርጫ ሥጋ ማከፋፈላቸውን የገለጸው፣ ይህ መልካም ተግባር የአዕምሮ እርካታ ይሰጣል ብሏል።
የከተማው ወጣቶች በዓልን የሌላቸውን ወገኖች በማሰብና አብሮነትን በሚያጠናክር መልኩ የማክበሩ ባህል እንደሚያጠናክርም ተናግሯል።
ሌላኛው ተሳታፊ ወጣት ሲሳይ አለበል በበኩሉ፤ በዓልን ከራስ ባለፈ ለሌላቸው ወገኖች በማካፈል በአብሮነት ማክበር ውስጣዊ እርካታን ያጎናጽፋል ብሏል።
በየበዓላቱ የሚያደርጉትን በጎ ተግባር በቀጣይም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጧል።
የገንዳ ውኃ ከተማ አስተዳደር ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ተስፋ መኮንን እንዳሉት፤ የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ብዙ ወገኖችን ከሀሳብ የታደገ አርአያነት ያለው ተግባር ነው።
በማዕድ ማጋራቱ 322 ወገኖች ድጋፍ እንደተደረገላቸው ገልጸው፣ በቅን አሳቢ ወጣቶች የሚከናወኑ በጎ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
በማዕድ ማጋራት ድጋፍ ከተደረገላቸው ወገኖች መካከል ወይዘሮ የሻረግ አስማረ በሰጡት አስተያየት በዓሉን ተደስተው እንዲያሳልፉ ድጋፍ ያደረጉላቸውን ወጣቶችና የተሳተፉ አካላትን አመስግነዋል።
በአቅም ማነስ ምክንያት ለበዓሉ ምንም ዝግጅት ሳያደርጉ ባዶ ቤት ተቀምጠው እንደነበር የገለጹት ወይዘሮዋ፣ በበዓል ወቅት የሚደረግ የእርስ በርስ መደጋገፍ አብሮነትን እንደሚያጠናክር ገልጸዋል።