ኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከደቡብ ሱዳን ጋር ትጫወታለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከደቡብ ሱዳን ጋር ትጫወታለች
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 4/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በ10ኛው የፊፋ ከ17 ዓመት ሴቶች የዓለም ዋንጫ የአፍሪካ ዞን ቅድመ ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታዋን ዛሬ ከደቡብ ሱዳን ጋር ታደርጋለች።
የሀገራቱ ጨዋታ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በጁባ ስታዲየም ይካሄዳል።
የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ራውዳ አሊ መጋቢት 14 ቀን 2018 ዓ.ም ለ23 ተጫዋቾች ጥሪ ባደረጉት መሰረት ተጫዋቾቹ ለማጣሪያው ጨዋታ ከመጋቢት 17 ቀን 2018 ዓ.ም አንስቶ በአዲስ አበባ ልምምድ አድርጓል።
በሀገር ውስጥ ከሚገኙ ክለቦች ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታዎችን አከናውኗል።
ቡድኑ የሀገር ቤት ልምምዱን አጠናቆ ሚያዚያ 2 ቀን 2018 ዓ.ም ጁባ ደርሷል።
ተጫዋቾቹ የመጨረሻ ልምምዳቸውን ትናንት በጁባ ስታዲየም ማድረጋቸውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
የቡድኑ ተጫዋቾች በሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኙም አመልክቷል።
የደቡብ ሱዳን ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሞሰስ ዛካሪያ ንጎር ለማጣሪያ ለ30 ተጫዋቾች ጥሪ ያደረጉ ሲሆን ቡድኑ በያዝነው ሳምንት በጁባ ልምምዱን ሲያደርግ ቆይቷል።
የሁለቱ ሀገራት የመልስ ጨዋታ በቀጣዩ ሳምንት በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
ኢትዮጵያ በደርሶ መልስ ውጤት ካሸነፈች በሁለተኛው ዙር ከማላዊ እና ብሩንዲ አሸናፊ ጋር ታደርጋለች።
10ኛው የፊፋ ከ17 ዓመት ሴቶች የዓለም ዋንጫ በሞሮኮ አስተናጋጅነት ከጥቅምት 7 እስከ ጥቅምት 28 ቀን 2019 ዓ.ም ይካሄዳል።
በውድድሩ ላይ 24 ሀገራት ይሳተፋሉ። በዓለም ዋንጫው አፍሪካ ሞሮኮን ጨምሮ በአምስት ሀገራት ትወከላለች።
በማጣሪያ የሚያልፉ አራት የአፍሪካ ሀገራት በሶስት ዙሮች በሚደረጉ ጨዋታዎች ይለያሉ።