ቀጥታ፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ለትንሳኤ በዓል ማዕድ አጋሩ

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 4/2018 (ኢዜአ)፦ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው የትንሳኤ በዓልን በማስመልከት ለተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች በአንድነት ፓርክ ማዕድ አጋርተዋል።


 

በመላው ኢትዮጵያ በክርስትና ጥላ ውስጥ በሚገኙ ቤተ-እምነቶች ያሉ ክርስቲያኖች የትንሳኤን በዓል በተስፋ፣ በመስዋዕትነት እና በአዲስ መነሳት መንፈስ በአንድነት እያከበሩ እንደሚገኙ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

ከሳምንታት የፆም፣ ጥሞና እና ራስን የመመልከት ጊዜ በኋላ ፋሲካ በእውነተኛ አምልኮ፣ መንፈስን አድሶ፣ ቤቶችንም በደስታ የሚሞላ መሆኑንና በዘመድ አዝማድ መጠያየቅ እንዲሁም ማዕድ መካፈል ፍቅርን የሚያዳብርበት መሆኑን ገልጿል።


 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ዓመታዊውን የፋሲካ የመዐድ ማጋራት ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በአንድነት ፓርክ በጋራ መታደማቸውን የጠቀሰው ጽህፈት ቤቱ፤ ይህም ለእውነተኛው የአንድነት መንፈስ ጉልህ ማሳያ መሆኑን አመልክቷል።

በዓለ ትንሳኤው በመላው ኢትዮጵያ የእምነት፣ ቤተሰባዊነት እና የመታደስ መንፈስ የሚታይበት ጊዜ መሆኑን በመጥቀስ፤ ሁላችንም በዚህ የትንሳኤ መንፈስ ዛሬም፣ ነገም፣ ሰርክ ቤታችንንና ልባችንን ለተቸገሩ ወገኖች እንድንከፍት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ጥሪውን በማስተላለፍ መልካም በዓል ተመኝቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም