የሀገር ባለውለታን መንከባከብ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሀገር ባለውለታን መንከባከብ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ነው
አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 4/2018 (ኢዜአ)፡-የሀገር ባለውለታ አረጋዊያንን መንከባከብ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ወይዘሮ ቡዜና አልከድር ገለጹ።
የ2018 ዓ.ም የትንሣኤ በዓል በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በታላቅ ድምቀት እየተከበረ ይገኛል።
በዓሉን በማስመልከትም የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ወይዘሮ ቡዜና አልከድር የወደቁትን አንሱ አረጋዊያን መርጃ ማዕከል ለሚገኙ አረጋዊያን ማዕድ አጋርተዋል።
በዚሁ ወቅትም ኢትዮጵያዊያን በዓላትን ሲያከብሩ የተቸገሩና አቅመ ደካማ ወገኖችን በማሰብ ሊያሳልፉ እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በበዓላት ወቅት ያለው ከሌለው ጋር በአብሮነትና መረዳዳት ማሳለፍም የኢትዮጵያዊያን የቆየ እሴት መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም የሀገር ባለውለታ አረጋዊያንን የመንከባከብ ሥራ የሁሉም ዜጋ የሞራል ግዴታ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የመዲናዋ ነዋሪዎችም አቅመ ደካማ ወገኖችን በማሰብ በመረዳዳትና መተሳሰብ ሊያሳልፉ እንደሚገባ ገልጸዋል።
የወደቁትን አንሱ አረጋዊያን መርጃ ማዕከል የሚጦሩ አረጋዊያን በበኩላቸው፤ በማዕድ ማጋራት መርሃ ግብሩ የወገናቸውን አስታዋሽነት በተግባር ያዩበት መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህም በማዕከሉ ተገኝተው የማዕድ ማጋራት የድጋፍ መርሃ ግብር ላደረጉላቸው ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።