31ኛው የዓለም አትሌቲክስ የርምጃ ሻምፒዮና ዛሬ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
31ኛው የዓለም አትሌቲክስ የርምጃ ሻምፒዮና ዛሬ ይካሄዳል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 4/2018 (ኢዜአ)፦ 31ኛው የዓለም አትሌቲክስ የርምጃ ሻምፒዮና ዛሬ በብራዚል ብራዚሊያ ከተማ ይደረጋል።
ሻምፒዮናው ከቀኑ 6 ሰዓት ከ45 አንስቶ ይካሄዳል።
ከ40 ሀገራት የተውጣጡ 333 አትሌቶች የሚሳተፉበት ይህ ሻምፒዮና፤ የማራቶን ርምጃ፣ የግማሽ ማራቶን ርምጃ እና ከ20 ዓመት በታች የ10 ኪሎ ሜትር የርምጃ ውድድሮችን በሁለቱም ጾታዎች ያካተተ ነው።
ኢትዮጵያ በዚህ ዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ትሳተፋለች።
በፓሪስ ኦሊምፒክ ተሳትፎው አመርቂ ውጤት ያስመዘገበው አትሌት ምስጋና ዋቁማ በ20 ኪሎ ሜትር የርምጃ ውድድር ሀገሩን ወክሎ የሚፎካከር ይሆናል።
በሴቶች ዘርፍ ደግሞ በአንጎላ እና ናይጄሪያ በተደረጉ የአፍሪካ ወጣቶች ሻምፒዮናዎች የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት የሆነችው አትሌት ህይወት አምባው በ10 ኪሎ ሜትር ውድድር ሀገሯን ትወክላለች።
በተጨማሪም በድሬዳዋ እና አዲስ አበባ በተካሄዱ የወጣቶች ሻምፒዮናዎች አሸናፊ የሆነው አትሌት አብዱሰላም አብዱልወሀብ በወንዶች 10 ኪሎ ሜትር ለሜዳሊያ ፉክክር እንደሚያደርግ ይጠበቃል።
የልዑካን ቡድኑን በበላይነት የሚመሩት የፌዴሬሽኑ ተወካይ ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ይፍሩ ከቴክኒክ ቡድኑ ጋር በመሆን ወደ ብራዚል መጓዛቸው ይታወቃል።
ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በተሳተፈችባቸው አምስት የዓለም አትሌቲክስ የርምጃ ውድድሮች ምንም አይነት ሜዳሊያ አግኝታ አታውቅም።
በውድድሩ ለመጀመሪያ ጊዜ ሜዳሊያ ለማግኘት ሶስት አትሌቶች ኢትዮጵያን ወክለው ይወዳደራሉ።