የቼልሲ እና ማንችስተር ሲቲ የሳምንቱ ተጠባቂ የሊግ ጨዋታ - ኢዜአ አማርኛ
የቼልሲ እና ማንችስተር ሲቲ የሳምንቱ ተጠባቂ የሊግ ጨዋታ
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 4/2018 (ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 32ኛ ሳምንት ሶስተኛ ቀን ውሎ አራት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።
ምሽት 12 ሰዓት ከ30 ቼልሲ ከማንችስተር ሲቲ በስታምፎርድ ብሪጅ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ቼልሲ በ48 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃን ይዟል። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ማንችስተር ሲቲ በ61 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ሁለቱ ክለቦች በፕሪሚየር ሊጉ ሲገናኙ የአሁኑ ለ59ኛ ጊዜ ነው።
ከ58ቱ የሊግ ጨዋታዎች መካከል ቼልሲ በ27ቱ ድል ሲቀናው ማንችስተር ሲቲ 21 ጊዜ አሸንፏል። በቀሪ 10 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።
ቼልሲ በጨዋታዎቹ ላይ 78 ጎሎችን ሲያስቆጥር ማንችስተር ሲቲ 65 ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፏል።
ባለፉት አምስት የሊግ ግንኙነታቸው ማንችስተር ሲቲ ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ በሶስት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል።
ቼልሲ ለመጨረሻ ጊዜ ማንችስተር ሲቲን በሊጉ ያሸነፈው እ.አ.አ በ2021 ነው።
ጨዋታው ለሁለቱም ክለቦች ትርጉም ያለው ነው።
ቼልሲ ማሸነፍ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ለመሳተፍ በሚያደርገው ፉክክር ወሳኝ ሶስት ነጥብ ያስገኝለታል።
ማንችስተር ሲቲ ካሸነፈ ከሊጉ መሪ አርሰናል ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ስድስት ዝቅ ያደርጋል። በዋንጫ ፉክክሩ ወሳኝ ሶስት ነጥብ ያሰገኝለታል።
የሊጉ መሪ አርሰናል ትናንት በቦርንማውዝ 2 ለ 1 ተሸንፏል።
በሌላኛው መርሐ ግብር ኖቲንግሃም ፎረስት ከአስቶንቪላ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በሲቲ ግራውንድ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ኖቲንግሃም ፎረስት በ32 ነጥብ 16ኛ ደረጃን ይዟል። አስቶንቪላ በ54 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ማሸነፍ ኖቲንግሃም ፎረስት ከወራጅ ቀጠና ለመራቅ ያስችለዋል።
አስቶንቪላ ሶስት ነጥብ የሶስተኝነት ደረጃን ከማንችስተር ዩናይትድ እንዲረከብ ያስችለዋል። በሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎ ፉክክሩ ወሳኝ ሶስት ነጥብ ያስገኝለታል።
ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ሰንደርላንድ ከቶተንሃም ሆትስፐርስ በስታዲየም ኦፍ ላይት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ሰንደርላንድ በ43 ነጥብ 12ኛ ደረጃን ይዟል። ቶተንሃም ሆትስፐርስ በ30 ነጥብ 18ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
ባለሜዳው ሰንደርላንድ ማሸነፍ የአውሮፓ መድረክ ተሳትፎ ተስፋውን ማለምለም ያስችለዋል።
ባለፉት 13 የሊግ ጨዋታዎች ከድል የራቀው ቶተንሃም ሆትስፐርስ ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት ሶስት ነጥብ ማግኘት ግድ ይለዋል።
በአምስት ዓመት ውል ከሰሞኑ የቶተንሃም አሰልጣኝ የሆነው ሮቤርቶ ዴ ዘርቢ የመጀመሪያ ጨዋታውን ዛሬ ያደርጋል።
ክሪስታል ፓላስ ከኒውካስትል ዩናይትድ ከቀኑ 10 ሰዓት በሰልኸረስት ፓርክ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።