ቀጥታ፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እየተከናወኑ የሚገኙ ሰው ተኮር የልማት ስራዎች በላቀ ትጋት ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው - ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል

አሶሳ፤ ሚያዚያ 3/2018 (ኢዜአ)፦ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እየተከናወኑ የሚገኙ ሰው ተኮር የልማት ስራዎች በላቀ ትጋት ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ተናገሩ።

ሚኒስትሯ በክልሉ እየተከናወኑ የሚገኙ የኮሪደር ልማት ስራዎችንና የልማት ፕሮጀክቶችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

ከጉብኝቱ በኋላ በሰጡት ማብራሪያ እንደገለፁት፤ መንግስት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚያከናውናቸው የልማት ፕሮጀክቶች በፈጠራና ፍጥነት እየተከናወኑ ይገኛሉ።

በአሶሳ እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት የከተማዋን ውብ ገፅታ ከማላበሱ ባለፈ ዘመናዊ  ከማድረግ አንጻር የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።

የአሶሳ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የስራ እንቅስቃሴን የጎበኙት ሚኒስትሯ ኮሌጁ አካባቢውን መሠረት ያደረገ የፈጠራ ስራ ላይ በመሠማራት ህብረተሰቡ የአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ተጠቃሚ ለማድረግ የጀመረውን የተግባር ስራ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አመላክተዋል።

ኮሌጁ ከመማር ማስተማር ባለፈ ክህሎት ሽግግርና ስራ ዕድል ፈጠራ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የገለፁት ሚኒስትሯ የቴክኒክ እና ሙያ ተቋማት ከህሎት መር እሳቤን ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ሚኒስትሯ በተጨማሪም በአሶሳ ከተማ የሚገኘውን የግራናይት ፋብሪካ የስራ እንቅስቃሴ የተመለከቱ ሲሆን ፋብሪካው በአካባቢው የሚገኘውን የግራናይት ማዕደን እሴት ተጨምሮበት ለገበያ እንዲውል በማድረግ እያከናወነ የሚገኘው ጅምር ተግባር የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።

ሚኒስትሯ በሆሞሻ ወረዳ የሚገኘውን የፍቃዱ ነመራ የተቀናጀ የእርሻ ልማት ድርጅት፣ የገጠር ኮሪደር ልማት እና ሌሎች የልማት ስራዎችን የጎበኙ ሲሆን በክልሉ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎች በላቀ ትጋት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።

በጉብኝቱ ላይ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻደሊ ሀሰንን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም