በአርባምንጭ ከተማ ለትንሳኤ በዓል የግብርና እና ሌሎች የፍጆታ ምርቶች በስፋት ቀርበዋል - ኢዜአ አማርኛ
በአርባምንጭ ከተማ ለትንሳኤ በዓል የግብርና እና ሌሎች የፍጆታ ምርቶች በስፋት ቀርበዋል
አርባምንጭ፤ ሚያዝያ 3/2018 (ኢዜአ)፦ በአርባምንጭ ከተማ ለትንሳኤ በዓል የግብርና እና ሌሎች የፍጆታ ምርቶች በስፋት ለገበያ መቅረባቸውን ሸማቾችና ነጋዴዎች ገለጹ።
ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አስተያየታቸውን የሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎችና ነጋዴዎች እንደገለጹት፤ የበዓል ገበያውን ለማረጋጋት የሚያስችሉ የተለያዩ ምርቶች በበቂ ሁኔታ ቀርበዋል።
ከሸማቾቹ መካከል አቶ ግዛቸው ጊዶሌ የዘንድሮው የፋሲካ በዓል የፋብሪካና የግብርና ምርቶች በበቂ ሁኔታ የቀረቡበት መሆኑን ጠቅሰዋል።
በተለይም በከተማው የሚገኙ የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ምርቶችን በቅናሽ ዋጋ በማቅረብ ረገድ ያላቸው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ሌላው አቶ አማኑኤል አስጨናቂ በዘንድሮው ገበያ ላይ የተወሰነ የዋጋ ጭማሪ ቢታይም፣ የምርት አቅርቦቱ አስተማማኝ በመሆኑ ሁሉም ሸማች እንደ አቅሙ መግዛት የሚችልበት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ተናግረዋል።
ነዋሪው ከሰንበት ገበያዎች የመገብየት ልምዱን ሊያዳብር እንደሚገባም መክረዋል።
በከተማዋ የሚገኙ የሰንበት ገበያ ማዕከላት ምርቶችን ከመደበኛው ገበያ ባነሰ ዋጋ እያቀረቡ መሆኑ የብራዘርስ ሰንበት ገበያ ማዕከል የሽያጭ ባለሙያዋ ታሪኳ ወሰቶ ተናግራለች።
በተለይም ነጭና ቀይ ሽንኩርት፣ ቲማቲም እንዲሁም የተለያዩ የፋብሪካ ምርቶች ከመደበኛው ገበያ በረከሰ ዋጋ ለማህበረሰቡ እየቀረቡ ነው።
የኤልያስ አየለ ሰንበት ገበያ የማዕከሉ ባለቤት አቶ ኤልያስ አየለ በበኩላቸው፤ ነዋሪው ለበዓልም ሆነ ለአዘቦት ቀናት እንዳይቸገር ጤፍ፣ በቆሎ፣ ስንዴ እና ማሽላን ጨምሮ ሌሎች የግብርና ምርቶችን በስፋት እያቀረቡ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በአርባምንጭ ከተማ እየተስፋፉ የመጡት የሰንበት ገበያዎች በሸማቹና በምርት አቅራቢው መካከል ያለውን ደላላ በማስቀረት፣ በዓሉ በዝቅተኛ ወጪ እንዲከበር ትልቅ እገዛ እያደረጉ መሆኑ ተመላክቷል።