ቀጥታ፡

ባሳለፍነው ሳምንት …

ከመጋቢት 27 እስከ ሚያዝያ 3 ቀን 2018 ዓ.ም ከተከናወኑ ዐበይት ጉዳዮች መካከል ፦

• ለትንሣኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት፤ የትንሣኤ በዓል በክርስቲያኖች ዘንድ ልዩ ቦታ ያለው በዓል ነው፤ ሞት የተሻረበትና ሕይወት ዋስትና ያገኘበት ነው ብለዋል።

የትንሣኤ በዓል ከሞት ባሻገር ሕይወት ከመቃብር ባሻገር ትንሣኤ መኖሩ የታወጀበት መሆኑንም ገልፀው፤ ሞት መጨረሻ መቃብር መዳረሻ አለመሆናቸው የተረጋገጠበት ነው ብለዋል በመልዕክታቸው።

የዘንድሮውን ትንሣኤ የምናከብረው ሀገራችን ኢትዮጵያ በሚያልፍ ፈተና ውስጥ እንዳለች እያሰብን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መንገዳችን ረጅም፣ ጉዟችን ፈታኝ መሆኑን እናውቃለን ሲሉ ገልፀዋል።

ብርሃን እንዳናይ የሚጋርዱ በጥልቁ ጨለማ ጠፍተን እንድንቀር አሥረው ለመያዝ የሚሞክሩ ወጥመዶች ብዙ ናቸው፤ ወደ ተስፋ ምድር እንዳንሻገር የሚጎትቱ ሰበቦች ሞልተዋል፤ ዳሩ ግን ከሕማማቱ ወዲያ ትንሣኤ ከዕንቅፋቱ ባሻገር ስኬት እንደሚጠብቀን አምነን እንታገላለን ሲሉም አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ ወደ ትንሣኤ መቃረቧን ገልፀው፤ የኢትዮጵያ ትንሣኤ ከሚበሰርባቸው ምዕራፎች አንዱ ግንቦት ላይ የሚካሄደው ምርጫ መሆኑንም አመላክተዋል።

ትንሣኤን ያለ ሕማማት እንደማናስበው ሁሉ ዴሞክራሲንም ከውጣ ውረድ ነጥሎ ማየት አይቻልም ብለዋል።

• የቡሩንዲው ፕሬዚዳንት በኢትዮጵያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሁለት ቀናት በኢትዮጵያ ጉብኝት ካደረጉት የቡሩንዲው ፕሬዚዳንት ኢቫሪስቴ ንድያይሺሚዬ ጋር ውጤታማ የሁለትዮሽ ውይይት ማድረጋቸውን ባሳለፍነው ሳምንት ገልጸዋል።

በዚሁ ወቅትም በተለያዩ ዘርፎች ያለንን ትብብር ለማጠናከር ያለሙ በርካታ የመግባቢያ ሰነዶች ፊርማ አከናውነናል ሲሉም አስታውቀዋል። ስምምነቶቹ ለሁለቱም ሀገራት የበለጸገ እና የተባበረ መጻኢ ዕድልን የሚያረጋግጡ የቆዩ ግንኙነቶቻችንን ወደ ተጨባጭ ትብብር ለመቀየር እንደ ወሳኝ መሠረት የሚያገለግሉ የጋራ ቁርጠኝነታችን ማሳያ ጭምር ናቸው ብለዋል።

ጉብኝታቸውን እንዳጠናቀቁም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተገኝተው ሸኝተዋቸዋል።

• ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

ባሳለፍነው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከአፍሪኤግዚም ባንክ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ኢሎምቢ (ዶ/ር) ጋር ተወያይተዋል።

በዚሁ ወቅትም ስትራቴጂካዊ ግንኙነታችንን በምናጠናክርባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረናል ብለዋል።

• የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አሥተዳደር ዓመታዊ አፈጻጸም ግምገማ

ባሳላፍነው ማክሰኞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አሥተዳደር ፕሬዚዳንት ሌፍተናንት ጄኔራል ታደሰ ወረደ ዓመታዊ የአፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦላቸው በውጤቶቹ ላይ ግምገማ እና ውይይት አድርገዋል።

• የሌፍተናንት ጄኔራል ታደሰ ወረደ ሹመት መራዘም

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 62(9) እና በዐዋጅ ቁጥር 359/1995 አንቀጽ 14 ንዑስ አንቀፅ 2(ለ) መሠረት የትግራይ ክልል አካታች ጊዜያዊ አሥተዳደርን በርዕሰ መሥተዳደርነት እንዲመሩ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የትግራይ ክልል አካታች ጊዜያዊ አሥተዳደር አስመልክቶ በጸደቀው ደንብ ቁጥር 479/2013 አንቀጽ 4(2) እና የዓመቱን የሥራ አፈጻጸም ባቀረቡት መሠረት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሚያዝያ 1 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ የሌፍተናንት ጄኔራል ታደሰ ወረደን ሹመት ለአንድ ዓመት አራዝመዋል።

• ማዕድ ማጋራት

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መጪውን የፋሲካ በዓል ምክንያት በማድረግ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች እና ጽሕፈት ቤቱ ለሚያሳድጋቸው ሕጻናት ማዕድ አጋርተዋል።

• የአምባሳደር ቆንጂት ሥነ ጊዮርጊስ ኅልፈተ ሕይወት

አምባሳደር ቆንጅት፤ በዲፕሎማሲው መስክ ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ ላበረከቱት ጉልኅ አስተዋጽዖ፣ ለሰጡት አስተምኅሮና ለነበራቸው ብልኅ አመራር ምንጊዜም ሲታወሱ እንደሚኖሩ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ባስተላለፉት የኀዘን መግለጫ መልዕክት ገልጸዋል። ትጉኅና ከብረት የጠነከሩ ዲፕሎማት ነበሩ በማለት ለሙያቸው የነበራቸውን ጽኑ አቋምና የሀገር ፍቅር ስሜትም አንስተዋል።

ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ኢትዮጵያን በዲፕሎማሲው መስክ ያገለገሉት አምባሳደር ቆንጂት በማረፋቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተሰማቸውን ኀዘን ገልጸዋል። አምባሳደሯ ለሕግ፣ ለአሠራር፣ ለፕሮቶኮል እና ለኢትዮጵያ ጥቅሞች በነበራቸው የጸና አቋም እናስታውሳቸዋለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከእርሳቸው በኋላ አያሌ ሴት ዲፕሎማቶች በመስኩ እንዲሠማሩ መንገዱን አስፍተዋል ብለዋል።

በተመሳሳይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ባስተላለፉት የኀዘን መግለጫ መልዕክት፤ በኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ታሪክ ውስጥ የማይረሳ እና ታላቅ ዐሻራን ማሳረፍ የቻሉት አምባሳደር ቆንጂት ሥነ ጊዮርጊስ ከዚህ ዓለም በሞት በመለየታቸው ጥልቅ ኀዘን ተሰምቶኛል ብለዋል። አምባሳደር ቆንጂት እስከ ከፍተኛ ዲፕሎማትነት በደረሰ ረጅም የሥራ ዘመናቸው ለሀገራችን ብሔራዊ ጥቅም ያስመዘገቡት ድል እና ያበረከቱት አስተዋጽዖ ሁልጊዜም በክብር የሚታወስ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት “ፖሊሳዊ አንድነት ለዘላቂ ሰላም” በሚል መሪ ሐሳብ 20ኛው የፖሊስ ኮሚሽነሮች መክፈቻ ጉባዔ ተካሂዷል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በዚሁ ወቅት፤ የመደመር መንግሥት የኢትዮጵያ ፖሊስ በሚሰጠው አገልግሎት ታማኝም አሳማኝም መሆን አለበት ብሎ ያምናል ብለዋል።

የፖሊስ ኃይላችን የጥፋት ኃይሎች በሀገራችንና በሕዝባችን ላይ የሰነዘሩትን ጥቃት በአንድነት በመቆምና መስዋዕትነት በመክፈል ቀልብሷል፤ ይህም ለሁላችንም ኩራት ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የፖሊስ አመራሮችና የሠራዊቱ አባላት በዕውቀት፣ በታማኝነትና በሕዝብ አገልጋይነት ሥነ-ልቦና ለላቀ ተልዕኮ እንድትዘጋጁ አደራ እላለሁ ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም