ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ለትንሣኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ - ኢዜአ አማርኛ
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ለትንሣኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 3/2018 (ኢዜአ)፦ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ለኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው፣ የትንሣኤ በዓል አራት ዋና ዋና ነገሮች ማለትም ሞት፣ መግነዝ፣ መቃብር እና ማኅተም የተሻሩበት ታላቅ ዕለት መሆኑን ገልጸዋል።
ሞትና መቃብር ከአዳም የመጡ የሰው ልጅ ዕዳዎች መሆናቸውን ጠቅሰው፣ መግነዝ በወዳጅ፣ ማኅተም ደግሞ በጠላት የሚደረጉ ተግዳሮቶች እንደሆኑ አስረድተዋል።
ሰው በአራቱም ፈተናዎች እንደሚገጥመውና ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የአዳምን የሞትና የመቃብር ዕዳ፣ የነዮሴፍን መግነዝ እንዲሁም የነቀያፋን ማኅተም ሽሮ ትንሣኤውን ማወጁን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያም ያለፈ ዘመን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ዕዳ እንዳለባት ያነሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እነዚህን ችግሮች መሻር ሲያቅታቸው ወዳጆች ያለበሱንን የፖሊሲና የስትራቴጂ መግነዝ እንዲሁም ጠላቶች ከዕዳ እንዳንወጣ ያተሙብንን ማኅተም እንሰብራለን ብለዋል።
ሀገራዊ ዕዳዎችን በሀገራዊ ምክክር፣ በሽግግር ፍትሕ እና በተሐድሶ ፕሮግራሞች ለመሻር መንግሥት እየሠራ መሆኑን የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ መግነዝ የተባሉትን የፖሊሲ ችግሮች በሪፎርሞች እንደሚያቃልሉና የተዘጋብንን በር በመክፈት ማኅተሙን እንደሚመክን አስታውቀዋል።
የትንሣኤ ብርሃን በእኩለ ሌሊት እንደመጣ በማስታወስ፣ የሀገሪቱ ትንሣኤም ለነቁና ለተዘጋጁ ዜጎች የሚታይ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሌሊታችን የመጣ ለመሰላቸው ሁሉ፤ ለእኛ ግን ትንሣኤያችን መሆኑን እናውጃለን በማለት መላው ኢትዮጵያውያን በዓሉን በንቃትና በተስፋ እንዲያከብሩ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።