ቀጥታ፡

ትንሳኤን የመሰሉ በዓላት የመደጋገፍና የአብሮነት እሴቶቻችንን አጠናክረን የምናስቀጥልባቸው ሊሆኑ ይገባል

መቱ ፤ሚያዝያ 3/2018 (ኢዜአ):- ትንሳኤን የመሰሉ ሃይማኖታዊ  በዓላት የሕብረተሰቡን የኖረ የመደጋገፍና የአብሮነት እሴቶችን አጠናክረን የምናስቀጥልባቸው ሊሆኑ እንደሚገባ ተገለጸ።

የመቱ ከተማ አስተዳደር የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ 240 ለሚሆኑ አቅመ ደካማ ወገኖች ማዕድ የማጋራት መርሃ ግብር አከናውኗል። 

በወቅቱም የከተማዋ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ካሳሁን ጉደታ እንደገለፁት፤ በማዕድ ማጋራቱ አካል ጉዳተኞችና ድጋፍ የሚሹ አረጋውያን እንዲሁም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ተካተዋል። 

ትንሳኤን የመሰሉ በዓላት የመደጋገፍና የአብሮነት እሴቶቻችንን አጠናክረን የምናስቀጥልባቸው ሊሆኑ እንደሚገባ አመልክተዋል። 


 

የማዕድ ማጋራትና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት የሕብረተሰቡን የመረዳዳትና የአብሮነት እሴቶች እያሳደጉ መሆናቸውንም ነው አቶ ካሳሁን የገለጹት። 

የመቱ ከተማ ማህበራዊ ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ሀምዝያ ታምሩ በበኩላቸው በዓላት የአንድነት፣ የፍቅር፣ የመተሳሰብና የመደጋገፍ እሴቶቻችንን በማጉላት ረገድ ሚናቸው የጎላ ነው ብለዋል።

የትንሳኤን በዓል ስናከብርም አብሮነታችንንና ድጋፋችንን ከሚሹ ወገኖች ጋር ሊሆን ይገባል ነው ያሉት። 

ማዕድ ከተጋሩት መካከል ወይዘሮ እጅጋየሁ ቶላ እና ወይዘሮ ፈጠነች በላይ ባገኙት ድጋፍ መደሰታቸውን ገልጸው ያገኙት ድጋፍ በዓሉን በደስታ ለማሳለፍ እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል። 

በዓሉን በደስታ ለማሳለፍ ድጋፍ ላደረገላቸው አካልም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም