የትንሳኤ በዓልን በመረዳዳትና ለሀገር ሰላም በመስራት ማሳለፍ ይገባል- የሃይማኖት አባቶች - ኢዜአ አማርኛ
የትንሳኤ በዓልን በመረዳዳትና ለሀገር ሰላም በመስራት ማሳለፍ ይገባል- የሃይማኖት አባቶች
ጎንደር፣ ገንዳውኃ፣ ሚያዝያ 3/2018 (ኢዜአ):- የትንሳኤ በዓልን በመረዳዳትና ለሀገር ሰላም በመስራት ማሳለፍ እንደሚገባ የሃይማኖት አባቶች አስገነዘቡ።
የሃይማኖት አባቶቹ እንዳመለከቱት ህዝበ ክርስቲያኑ የትንሳኤ በዓልን በመረዳዳትና ለሀገር ሰላም በመስራት መሆን አለበት።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀ ዻዻስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ዮሐንስ ባስተላለፉት መንፈሳዊ መልእክት ምዕመኑ የትንሳኤ በዓልን ሲያከብር ሃይማኖታዊ አስተምህሮውን በመተግበር መሆን አለበት ብለዋል።
በዚህም የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳትና ለሀገር ሰላምና አንድነት በመስራት መሆን እንደሚገባውም ተናግረዋል፡፡
በጎንደር ከተማ የሃገር ሽማግሌ አባ ብርሃኑ ተስፋዬ በበኩላቸው ህዝበ ክርስቲያኑ የትንሳኤ በዓልን ሲያከብር ካለው ላይ በመቀነስ ለአቅመ ደካማ ወገኖች በማካፈል ሊሆን እንደሚገባ አመልክተዋል።
በበዓሉ ወቅት ሃይማኖታዊ ግዴታ የሆነውን በጎነትና መተሳሰብ አጠናክረን መቀጠል አለብን ብለዋል።
የትንሳኤ በዓል ያለው ለሌለው የሚያካፍልበት ነው ያሉት ደግሞ ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ አድማሴ ደሞዝ ናቸው፡፡
በዓሉ አብሮነታችንን የምናጠናክርበት እንዲሁም ለአገራችን ሰላምና አንድነት የምንተጋበት መሆን እንዳለበትም መክረዋል።
በተመሳሳይም የምዕራብ ጎንደር ዞን ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ አእላፍ ቆሞስ አባ ኃይለ ማርያም ያሳይ፤ በበኩላቸው ትንሳዔ ለሰው ልጆች ደህንነትና ፍቅር ሲባል ህይወት የተከፈለበት በዓል መሆኑን ገልጸዋል።
በዓሉን ስናከብርም ፍቅርን፣ ሰላምንና ትህትናን በመላበስ ለሀገር ሰላምና አንድነት አበክሮ በመስራት ሊሆን ይገባል ብለዋል።
በዓሉን ያላቸው ለሌላቸው በማካፈልና በይቅርታ ማሳለፍ እንደሚገባም አስረድዋል።
በዓሉን ስናከብር የተቸገሩትን በመርዳትና አብሮነትን በማጠናከር መሆን እንዳለበት የተናገሩት ደግሞ በሀገረ ስብከቱ የትምህርትና ስልጠና ክፍል ኃላፊ መጋቢ ሀይማኖት ፍሬአሚን ጌቴ ናቸው።
ምዕመኑ በዓሉን ሲያከብር ለሌሎች ሰዎች ሰላምና ደስታ የሚሰጡ ተግባራትን በመፈጸም መሆን አለበት ብለዋል።