ቀጥታ፡

በጂንካ ከተማ በትንሳዔ በዓል ገበያ በቂ የእርድ እንስሳት ቀርበዋል

 ጂንካ፣ ሚያዝያ 3/2018 (ኢዜአ) ፡- በጂንካ ከተማ በትንሳዔ በዓል ገበያ በቂ የእርድ እንስሳት አቅርቦት መኖሩን ሸማቾች ተናገሩ።

እንደ ሸማቾቹ ገለጻ፤ ለበዓሉ የሚሆኑ የእርድ ሰንጋዎች፣ ፍየሎችና ዶሮዎች በስፋት ለገበያ ቀርበዋል።   


 

በበዓል ገበያ ሲሸምቱ ያገኘናቸው የጂንካ ከተማ ነዋሪው አቶ በሃይሉ መንግስቱ እንደገለጹት፣ ለበዓሉ የሚሆኑ የተለያየ ደረጃ ያላቸው ሰንጋዎች በየዋጋ አማራጫቸው ቀርበዋል።   


 

በተለይም በቂ የእርድ እንስሳት አቅርቦት በመኖሩ፣ ለሸማቹ በሚፈልገውና በአቅሙ ልክ መቅረብ መቻሉን ነው የተናገሩት።   

በገበያው የእርድ እንስሳት አቅርቦት በበቂ ሁኔታ መኖሩን የገለጹት ደግሞ ሌላኛው ሸማች አቶ ሳሙኤል ቻለው ናቸው፡፡ 

በገበያው አቅርቦቱ በአማራጭ መቅረብ በመቻሉ ሁሉም አቅሙን ባገናዘበ መልኩ ሸምቶ በዓሉን እንዲያከብር አስቻይ ሁኔታ ስለመፈጠሩም አመልክተዋል።


 

በገበያው ላይ የሚታየውን የሰንጋ፣ የፍየልና የበግ እንዲሁም የዶሮ የዋጋ ሁኔታ በተመለከተ አስተያየታቸውን የሰጡት ሸማቾቹ፣ ከአቅርቦት አንጻር ችግር ባይኖርም የዋጋ ጭማሪ መታየቱን ጠቁመዋል።   

የጂንካ ከተማ ንግድና ገበያ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሀብታሙ ሐዝሚ በበኩላቸው በገበያው የምርት አቅርቦት እጥረት እንዳይኖር እና ያለአግባብ ምርት ላይ ዋጋ እንዳይጨመር ግብረ ሃይል ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን  ተናግረዋል፡፡


 

በከተማው የግብርና ምርትም ሆነ የእርድ እንስሳት በቂ አቅርቦት በመኖሩ ሸማቹ የአቅሙን ያህል ገዝቶ በዓሉን ለማሳለፍ  አስቻይ ሁኔታ አለ ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም